ባለፉት አስር ቀናት ከ80 ኪሎ ሜትር በላይ የኮንዳክተር ሽቦ ገመድ እና 25 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የኦ.ፒ.ጂ ደብሊው ፋይበር መስመር ለስርቆት መዳረጋቸውን የአዋሽ – ወልዲያ – ሃራ ገበያ የባቡር የኃይል አቅርቦት ፕሮጀክት ቢሮ አስታወቀ።
በቢሮው የሳይት ሥራ አስኪያጅ አቶ ተክለወይን ብርሃነአሰፋ እንደተናገሩት ባለፉት አስር ቀናት ከመተሃራ እስከ ባቡር ትራክሽን ጣቢያ አንድ ድረስ በቡድን በተደራጀ ሁኔታ 78 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር የኮንዳክተር ሽቦ እና 25 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የኦፕቲካል ፋይበር መስመር ዝርፊያ ተፈጽሟል።
ከባቡር ትራክሽን ጣቢያ አንድ እስከ ባቡር ትራክሽን ጣቢያ ሁለት ድረስ ደግሞ 2 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የኮንዳክተር ሽቦ ገመድ በዘራፊዎች መወሰዱንም ነው አቶ ተክለወይን የጠቆሙት።
በአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ በዱዱብ እና ዶሆ ቀበሌዎች ሁለት ጊዜ እንዲሁም በዱለሳ ወረዳ በቡሩቱሊ እና ኢስኪለሊ ቀበሌዎች አንድ ጊዜ በተፈፀመ የስርቆት ወንጀል ሳቢያ ከ758 ሺህ ዶላር በላይ እና በብር ከ6 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ መድረሱን ተናግረዋል።
የስርቆት ወንጀሉ የተፈፀመው የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ ወደ ሥራ እስኪገባ ድረስ በ33 እና 15 ኪሎ ቮልት በጊዜያዊነት ኃይል ይዞ እንዲቆይ ለማድረግ ከሥራ ተቋራጩ ጋር ምክክሮች እየተደረጉ ባሉበት ወቅት መሆኑ እንዳሳዘናቸውም ገልፀዋል።
እንደ ሳይት ሥራ አስኪያጁ ገለፃ ዝርፊያ ተፈፅሞባቸው በአይሱዙ መኪና ተጭነው ሲጓዝ የነበረ የኮንዳክተር ሽቦ በአዳማ ከተማ ላይ እንዲሁም በዱለሳ ወረዳ መቁረጫ ሴጌቶ ይዘው የተገኙ ሁለት ተጠርጣሪዎች ተይዘው ክስ ለመመስረት ማስረጃ እየተደራጀ ይገኛል ብለዋል፡፡
በኃይል መሰረተ ልማት ስርቆት ዙሪያ ከዞን፣ ከወረዳ እና ከቀበሌ አመራሮች እንዲሁም ከፀጥታ ዘርፍ አካላት ጋር ውይይት ከተደረገ በኋላ ከ2 ኪሎ ሜትር በላይ የኮንዳክተር ሽቦ በዘራፊዎች መወሰዱን አብራርተዋል።
በተቋሙ የኃይል መሰረተ ልማት ደህንነት፣ ክትትልና ቁጥጥር ሥራ አስኪያጅ አቶ ዋለ ታምሬ እንደተናገሩት በፕሮጀክቱ ላይ የተፈፀመው የስርቆት ወንጀል እጅግ አስደንጋጭ ነው።
በበጀት ዓመቱ በኦፕሬሽን ላይ የሚገኙ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ ይፈፀሙ የነበሩ የስርቆት ወንጀሎች መቀነሳቸውን የገለፁት ሥራ አስኪያጁ ይሁን እንጂ በግንባታ ላይ ባሉ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ ስርቆቱ መቀጠሉን ተናግረዋል።
በአዋሽ- ወልዲያ-ሃራ ገቢያ ላይ የተፈፀመው ዝርፊያ በሀገር ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና የሚያሳድር ከመሆኑም ባሻገር ተቋሙ የኃይል ተደራሽነትን ለማሳደግ በሚያከናውናቸው ሥራዎች ላይ እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል ስጋታቸውን መግለጻቻን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል አስታውቋል፡፡
ምላሽ ይስጡ