የናይል ተፋሰስ አባል ሀገራት የውሃ ሚኒስትሮች የዓባይ ግድብ ጉብኝት ለሚኒስትሮች ጥያቄ ምላሽ የሰጠ ነው ሲሉ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) አስታወቁ። በዓባይ ግድብ ላይ በሚኒስትሮቹ የተካሄደው ጉብኝት በኢትዮጵያ ተቃራኒ የቆመውን አካል ያሽመደመደ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የተፋሰሱ አባል ሀገራት ወደ ናይል ቀን ስብሰባ ሲመጡ እግረ መንገዳቸውን የዓባይ ግድብንም እንዲጎበኙ አስቀድማ ደብዳቤ ልካለች። በአንጻሩ የግብፁ የውሃ ሚኒስትር ለሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት ሚኒስትሮች በኢትዮጵያ በኩል የተላለፈላቸውን የዓባይ ግድብን ጎበኙ ጥሪ መቀበል የለባችሁም ሲሉ በደብዳቤ ገልጸዋል። ይሁንና ሚኒስትሮቹ የግብፅን ጥሪ ባለመቀበል የዓባይ ግድብን ጎብኝተው ከሰማይ በታች፤ ከምድር በላይ አለኝ የሚሉትን ጥያቄዎቻቸውን ሁሉ ጠይ ቀው ምላሽ ማግኘት ችለዋል።
እኛ በደብዳቤ ለታጀበው የግብፅ የ”አትጎብኙ” መልዕክት የመልስ ምት አልሰጠንበትም ያሉት ሚኒስትሩ፣ ጉዳዩ የተለመደ የሐሰት ፕሮፖጋንዳቸው አካል እንደመሆኑ ንቀን አልፈነዋል ብለዋል። ይሄ ደግሞ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን፣ የተፋሰሱ ሀገራት የውሃ ሚኒስትሮችም ምላሽ ሳይሰጡበት ያለፉት ጉዳይ መሆኑንም ገልጸዋል።
እንደ ኢንጂነር ሀብታሙ (ዶ/ር) ገለጻ፤ የዓባይ ግድብ እንዳይጎበኝ በግብፁ የውሃ ሚኒስትር የቀረበው ጥያቄ ትርጉሙ ለሌሎች የተፋሰሱ ሀገሮች ያላቸውን ንቀት ማሳያ ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ግድቧን ለማስጎብኘት መጋበዝ መብቷ እንደሆነ ሁሉ፤ እነርሱም የኢትዮጵያን ግብዣ መቀበል አለመቀበል መብታቸው ነው።
በዚህ ረገድ በመጀመሪያም ቢሆን የዓባይ ግድብን እንዲጎበኝ የጋበዘችው ኢትዮጵያ እንጂ የናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ፤ የግብፁ የውሃ ሚኒስትር የአትጎብኙ መልዕክታቸውን ሲያስተላልፉም አንድም ሀገር እንዳልተቀበላቸው ተናግረዋል። “ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ትልቅ ስኬት ነው። ግብፅም በኢትዮጵያ ሜዳ ለመጫወት ፈልጋ በራሷ ላይ ግብ አስቆጥራለች፤ ይሄም የአደባባይ ምስጢር ለመሆን ችሏል።” ብለዋል። ይሄ ደግሞ ለግብፅ አላስፈላጊ ጥይት ተኩሳ እራሷን እንደማቁሰል የሚቆጠር ነው ብለዋል።
“አስገራሚው ነገር እንዳትሔዱ ብለው ያሏቸው ሚኒስትሮች ወደ ዓባይ ግድብ የሔዱት እንዲያውም በከፍተኛ ተነሳሽነት ነው። ለስብሰባው የመጡት በሙሉ (የታንዛኒያው የውሃ ሚኒስትር በሀገራቸው ከምርጫ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ባጋጠማቸው አስቸኳይ ሥራ ከመሄዳቸው በስተቀር) ሁሉም የዓባይ ግድብን በሚኒስትር ደረጃ ጎብኝተዋል። በጉብኝቱም ሁሉም ለነበራቸው ጥያቄ ምላሽ አግኝተውበታል።
ሚኒስትሮቹ ዓባይ ግድብ ከደረሱ በኋላ የነበራቸው አግራሞት በግልጽ የሚታይ ነበር ያሉት ሚኒስትሩ፤ ቀደም ሲል ሲነዛ የነበረው ፕሮፓጋንዳ እና መሬት ላይ ያዩት እውነታ ልዩነቱ አስደንቋቸዋል ብለዋል። ያንን የሚያክል ግድብ ኢትዮጵያ መገንባት መቻሏ እንደ ተዓምር የሚታይ ነው የሚል አስተያየትም መስጠታቸውንም ገልጸዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ ጎብኚዎቹ አንደኛ የግድቡ መጠን ከጠበቁት በላይ ሆኖባቸዋል። ስፋቱና የውሃ መጠኑ አስደምሟቸዋል። ከምንም በላይ የሥራው ጥራት ትንግርት ሆኖባቸዋል። ትልቁ ስኬት ያሉት ደግሞ ኢትዮጵያ የዓባይ ግድብን ለመገንባት ስትል ያለፈችው ፈተና የሚያስደነቅ ስለመሆኑም የጉብኝቱ ሚኒስትሮች አስተያየታቸውን አካፍለዋል።
በዚህም አንዳንዶቹም ተመልሰው ወደ ሀገራቸው ሲሔዱ እንዴት አድርገን ነው በሀገራችን ላይ ተመሳሳይ ፕሮጀክት የምንቀርጸው? የሚል ቁጭት ውስጥ መግባታቸውን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ ጉብኝቱ ለኢትዮጵያ ከፍ ያለ ድልን ሲያስገኝ በአንጻሩ ግብፆች ያደረጉት ዘመቻ መልሶ እነሱኑ የጎዳ መሆኑን ነው ያብራሩት።
ምክንያቱም ጎብኚዎቹ ግድቡን ገና እንዳዩት ከመደነቃቸው ባለፈ፣ ግብፆች ሲያራግቡት የነበረው ፕሮፓጋንዳ ሐሰት መሆኑን ተገንዝበዋል። አንዳንዶቹ ሚኒስትሮችም በሰሙትና ባዩት ነገር መለያየት ምክንያት በንዴት ውስጥ ሆነው ይናገሩ ነበር። “ይህን መሬት ላይ ያየነውን ጉዳይ ለየሀገሮቻችን መሪዎች ብንገልጽላቸው ምን ሊፈጠር እንደሚችል መረዳት ይቻላል፤” እያሉም በቁጭት ስሜት ሀሳባቸውን መግለጻቸውን ነው ሚኒስትሩ ያስረዱት።
ለዚህ ደግሞ ከሚመለከቱት እውነት ባሻገር ሚኒስትሮቹ በጉብኝቱ ወቅት ላነሷቸው ጥያቄዎች ከኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ጭምር ምላሽ መሰጠቱ ትልቅ መረዳትን ፈጥሮላቸዋል። እምነትንም አሳድሮባቸዋል። ይሄም ኢትዮጵያ በተፋሰሱ ሀገራት ዘንድ ግልጽነት የፈጠረችበትን አጋጣሚ የተፈጠረላት ሲሆን፣ ግብፅ ደግሞ ትልቅ ኪሳራ ያጋጠማት መሆኑን አብራርተዋል።
እንደ ኢንጂነር ሀብታሙ (ዶ/ር) ገለጻ፤ ከሁሉም ሀገራት የመጣው የቴክኒካል አደቫይዘሪ ኮሚቴ (Technical Advisory Committees) የሚባል ቡድን፣ መሬት ላይ ሲያዩት ግድቡን ለመግለጽ “ይህ ሜጋ ፕሮጀክት ነው፤ በአግባቡ ከውናችሁታል፤ በእናንተ ኩራት ይሰማናል፤ የኢትዮጵያ ክብር ደግሞ የአፍሪካም ኩራት ነው” ሲሉ ስሜታዊ ሆነው መናገራቸውንም ገልጸዋል። ሌሎች የጉብኝቱ ተሳታፊዎችም “ኢትዮጵያ ሁሌም መሪ ናት፤ እናንተ ኢትዮጵያን መገንባት ከጀመራችሁ ቆይቷችኋል” ማለታቸውንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል። በዚህ መሠረት የዓባይ ግድብ ጉብኝት በኢትዮጵያ ተቃራኒ የቆመውን አካል ያሽመደመደ ሆኖ አልፏል ሲሉ ማመልከታቸውን ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ጉብኝቱ፣ በተለይ ግብፅ ለሌላ ጊዜ የምትናገረውን ንግግር አስባበት እንድትናገር ያደረገ ጭምር ነው ብለዋል። ቀደም ሲል እንዲጎበኙ ታስበው የነበሩ ሃያ ሰዎች ቢሆኑም፤ ከግብፁ ሚኒስትር የአትጎብኙ ጥሪ በኋላ የሰው ቁጥር ወደ 30 ከፍ ማለቱም ለጉብኝቱ ከፍ ያለ ትኩረት የሰጡት መሆኑን የሚያመላክትም ነው ብለዋል።
ምላሽ ይስጡ