በህገ-ወጥነት ተግባር ላይ የተሰማሩ የነዳጅ ኩባንያዎች እና ማደያዎች ወደ ህጋዊነት እንዲገቡ ማሳሰቢያ መሰጠቱን የገለጹት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዶክተር ካሳሁን ጎፌ ናቸው፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከነዳጅ ኩባንያ ባለቤቶችና ኃላፊዎች ጋር በነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ዙሪያ ወይይት ማድረጉን አስታዉቀዋል፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዶክተር ካሳሁን ጎፌ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ዛሬ እንደገለፁት በነዳጅ ኩባንያዎች፣ በነዳጅ ማደያዎችና፣ በየደረጃው በሚገኙ የመንግስት አደረጃጀቶች በኩል ያሉ ውስንነቶች ላይ በግልጽ ተወያይተናል ብለዋል፡፡
በውይይቱም በህገ-ወጥነት ተግባር ላይ የተሰማሩ የነዳጅ ኩባንያዎች እና በስራቸው የሚገኙ ማደያዎች በፍጥነት ወደ ህጋዊነት እንዲገቡ በግልፅ አሳስበናል ሲሉ የገለፁት ሚኒስትሩ በበቂ መረጃ ላይ ተመስርተው ነዳጅን በህገ-ወጥ ችርቻሮ የሚሰራጭበትን መንገድ ለማስቆም ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
ነዳጅ ላይ የሚስተዋለው ህገ-ወጥ ንግድ በዋናነት ህዝቡን የሚጎዳና አንገብጋቢ ጉዳይ በመሆኑ መንግስት ይህን ችግር ለመፍታት አዋጅ አውጥቶ ለተግባራዊነቱ በቂ ዝግጅት ማድረጉንም ጠቁመዋል፡፡
አክለውም ሰው ሰራሽ የገበያ እጥረትን በመፍጠር ያልተገባ ትርፍ ለማግኘት የሚደረጉ ጥረቶችን እንደማይታገሱ ገልፀዋል፡፡
ከሰሞኑ በተለያዩ የሃገሪቱ አከባቢዎች የነዳጅ እጥረት እና ህገወጥ የነዳጅ ግብይቶች እየተስተዋሉ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ምላሽ ይስጡ