በቀን ከ150 ሺህ ሊትር በላይ ወተት እና የወተት ተዋፅኦ የማቀነባበር አቅም ያለው የሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ፣ በግብዓት እጥረት ምክንያት እስካሁን በቀን የሚያቀነባብረው መጠን ከ65 ሺህ ሊትር እንዳልተሻገረ ገልጿል፡፡
ለረጅም ዓመታት የማማ ወተትን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እያከፋፈለ ያለው ኢንዱስትሪው፣ ምርቱን ከቀድሞው በበለጠ መጠን ወደ ህብረተሰቡ ለማድረስ፣ የግብዓት እጥረት ከባድ ፈተና እንደሆነበት የሚናገሩት የሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ ይመር ናቸው፡፡
አርሶ አደሩ እና ወተት አቅራቢ ማህበራት በቂ የመኖ አቅርቦት አለማግኘታቸው እና የመኖ ዋጋ ተመጣጣኝ አለመሆን ለግብዓት እጥረቱ ዋና ምክንያት እንደሆነም ዋና ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡
ከ50ሺሕ በላይ አርሶ አደሮችን ይዘው የተደራጁ ከ15 በላይ ማህበራት አሁን ላይ ለኢንዱስትሪው ወተት እያቀረቡ ቢሆንም፣ የመኖ እጥረቱ ማህበራቱ የኢንዱስትሪውን ፍላጎት የሚያሟላ ወተት እንዳያቀርቡ አድርጓቸዋል ብለዋል፡፡
መንግስት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ባስጀመረው የሌማት ትሩፋት አርሶ አደሩ የተሻለ የመኖ አቅርቦት እና የወተት ምርት እንዲያገኝ ቢያስችለውም፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ወተት የሚሰጡ የላም ዝርያዎች ብዙ መኖ የሚፈልጉ በመሆናቸው እስካሁን ችግሩን ሙሉ በሙሉ መቅረፍ እንዳልተቻለ አቶ ሙሉጌታ ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደሩ የሚያጋጥመው የመኖ እጥረት ችግር እንዲቀረፍ ኢንዱስትሪው ወተት ከማቀነባበር ስራ ጎን ለጎን፣ በቅርቡ መኖ ማቀነባበር መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም በቀን ከ45 ሺህ ኩንታል በላይ መኖ ማቀነባበር የሚችል ማሽን ተተክሎ ወደ ስራ መግባቱን አክለዋል፡፡
የግብዓት እጥረት ችግርን ለመቅረፍ በቀጣይ ከአርሶ አደሩ እና ወተት አቅራቢ ማህበራት እንዲሁም ከሌሎች አካለት ጋር በመሆን ተጨማሪ የመፍትሄ አማራጮችን በመፈለግ እንደሚሰራ ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ ሙሉጌታ ይመር ተናግረዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ