ህፃናት ላይ የሚከሰተውን ፖሊዮ እና ተጓዳኝ በሽታዎችን ለመከላከል በዘመቻ መልክ የፖሊዮ ክትባት ሊሰጥ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል፡፡
የፖሊዮ ስርጭት በአለም አቀፍም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ አሳሳቢ መሆኑን እና ህፃናት ለተጓዳኝ በሽታዎች እንዳይጋለጡ የጥምር ዘመቻ የፖሊዮ ክትባት በሚል ከዛሬ ጀምሮ ለ4 ተከታታይ ቀናት እንደሚሰጥ ያስታወቁት በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የፖሊዮ ወረርሽኝ ምላሽ አስተባባሪ አቶ ሚኪያስ አላዩ ናቸው፡፡
የዘመቻ ክትባቱ ከዚህ ቀደም መደበኛ ክትባት የወሰዱም ሆነ ምንም ዓይነት ክትባት ያልጀመሩ ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ፣ በአማራ፣ አፋር እና ጋምቤላ ክልል መስከረም እና ታህሳስ ላይ በሁለት ዙር መሰጠቱን በመጥቀስ፤ በዚህኛው ዙር በ10 ክልሎች ለሚገኙ ከ13 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ህፃናት ለማዳረስ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡
በዘመቻ በሚሰጡ ክትባቶች ሌሎች ተጓዳኝ የሆኑ በሽታዎችን በመለየት ወደ ህክምና ተቋም እንዲያመሩ የሚደረግበት ሁኔታ መኖሩን በኢንስቲትዩቱ የፖሊዮ ወረርሽኝ ምላሽ አስተባባሪ አቶ ሚኪያስ አላዩ ገልፀዋል፡፡
ከዚህ ቀደምም ለኩፍኝ በሽታ በተሰጠ ዘመቻ የእግር መቆልመም በሽታ ያለባቸው ህፃናት ተለይተው ወደ ህክምና እንዲሄዱ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ማህበረሰቡ ስለበሽታው ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ ቢሆንም ኢንስቲትዩቱ በአለም አቀፍ ደረጃ የጤና ችግር መሆኑን በመለየት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ህፃናት የበሽታ መከላከል አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ መከተብ እንዳለባቸው የገለጸት አስተባባሪው፤ ወላጆች፣ አሳዳጊዎች እና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት ተባባሪ እንዲሆኑ ጠይቀዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ