በትግራይ ክልል ከየካቲት 14 እስከ 17/2017 ዓ.ም ድረስ ከአምስት አመት በታች ለሆኑ ህፃናት የፖሊዮ ክትባት እንደሚሰጥ የክልሉ ጤና ቢሮ አስታውቋል፡፡
ክትባቱ የሚሰጣቸው ከ800 ሺ በላይ የሚሆኑ ከ5 አመት እድሜ በታች ያሉ ህፃናት መሆናቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር በሪሁ መስፍን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ በመጠለያ ጣቢያ ተፈናቅለው የሚገኙ ህፃናትን ጨምሮ ሌሎቹንም ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡
በእነዚህ ተከታታይ ቀናት ሌሎች በሽታዎችን የማጥራት እና ህክምና የመስጠት ስራ እንደሚሰራ ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡ ክትባቱን ወደ ተለያዩ አከባቢዎች ተንቀሳቅሶ ለመስጠት ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት መኖሩን የገለፁት ዳይሬክተሩ ክልሉ አሁን ካለበት ወቅታዊ ሁኔታ አኳያ ተግዳሮት እንደሚፈጥርበት አስታውቀዋል፡፡
በክልሉ የሚከናወነው የፖሊዮ ክትባት በነዳጅ አቅርቦት ችግር ምክንያት እንዳይስተጓጎል እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በክልሉ የንግድና ሸማቾች ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ክንደያ ናቸው። በክልሉ የነዳጅ አቅርቦት ችግር ቢኖርም ለጤና አገልግሎት ቅድሚያ እንዲሰጥ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የጤና ባለሙያዎቹ ለፖሊዮ ክትባት ወደ ተለያየ ቦታዎች ስለሚንቀሳቀሱ በቀላሉ ነዳጅ እንዲያገኙ የሚያስችል አሰራር መቀመጡንም አመላክተዋል፡፡ በክልሉ የነዳጅ እና ናፍጣ አቅርቦት ችግር መኖሩን በመግለጽ፤ በዚህ ምክንያት ክትባቱ እንዳይስተጓጎል ከጤና ቢሮ ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በትግራይ ክልል ተፈናቃዮችን ጨምሮ ለአከባቢው ህጻናት ለቀጣይ ተከታታይ 4 ቀናት የፖሊዮ ክትባት የሚሰጥ በመሆኑ ማህበረሰቡ ህጻናትን እንዲያስከትብ የክልሉ ጤና ቢሮ ጥሪ አቅርቧል።
ምላሽ ይስጡ