ለአንድ ሳምንት ያህል በአርሲ የሚገኘው የጋለማ ደን በእሳት ውስጥ እንደሚገኝ ያስታወቀው የአርሲ ተራራሮች ብሄራዊ ፓርክ ነው፡፡
መናኸሪያ ሬዲዮ ያነጋገራቸው የፓርኩ ሃላፊ አቶ መሃመድ ቲፎ በደኑ ውስጥ ብርቅዬ የሆኑ የዱር እንስሳቶች በስፋት የሚገኙበት እንደሆነ አስታውቀው፤ከነዛም ውስጥ የደጋ አጋዘን፤ቀይ ቀበሮ ፤የሚኒሊክ ድኩላ እና ሌሎች የዱር እንስሳቶች እንዳሉ ይገልፃሉ፡፡ አንድ ሳምንት ሙሉ ደኑ ከፍተኛ የሆነ የእሳት አደጋ ውስጥ እንደሚገኝ ገልጸው ፤አሁንም ድረስ ምንም አይነት መፍትሄ ማግኘት እንዳልቻለም ነው ያስታወቁት፡፡ ደኑ ከዚህ ቀደም መሰል አደጋዎች በስፋት እንደሚገጥሙት አስታዉሰዉ ለተወሰነ ጊዜ ጋብ ብሎ የነበረዉ መሰል አሁን ዳግም መቀስቀሱን አስረድተዋል፡፡
አያይዘውም ከሰሞኑ በደኑ የታየውን እሳትን ተከትሎ ለእሳቱ መነሻ ምክንያት የሆኑ ተጠርጣሪዎችን መያዛቸውን እና በህግ አግባብ ተጠያቂ እንደሚደረጉም ተናግረዋል፡፡
እሳቱን ማጥፋት የሚቻልባቸውን መሳሪያዎች ለማግኘት ለኢትዮጵያ ደን ልማት በቃል ጥያቄ ማቅረባቸዉን የገለጹት አቶ መሃመድ ፤ይሁን እንጂ አጥጋቢ የሆኑ ምላሾች እየተገኙ እንዳልሆነ አስታውቀዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ደኑ ምን ያህል በእሳቱ ወድሟል የሚለውን ጉዳይ በጥልቀት ማወቅ እንዲቻል እና ማጥፋት የሚቻልባቸዉን ተጨማሪ አማራጮ ዙሪያ ምክክር እየተደረገ መሆኑን ገልጸዉ በተጨማሪም መሳሪያዎችን ለማግኘት በደብዳቤ ለኢትዮጵያ ደን ልማት ጥያቄ እንደሚቀርብ አስረድተዋል፡፡
በአርሲ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ስር እንደ ጭላሎ፤ካካ፤ሆንቆሎ እንዲሁም ጋላማ የተሰኙ ደኖች መኖራቸውን ይታወቃል፡፡ይሁን እንጂ ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ድረስ በደኑ ውስጥ ያለው እሳት አለመጥፋቱም ነው የተገለጸው፡፡
ምላሽ ይስጡ