በኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች መካከል ያለዉን አዎንታዊ ግንኙነት በሚያሳይ መልኩ እና በኤርትራ በኩል ያለውን ነባራዊ ጠብ ቀስቃሽ እንቅስቃሴ ብስለት በሚስተዋልበት ዲፕሎማሲያዊ እርምጃዎች ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ማጋለጥና ምላሽ መስጠትም ያስፈልጋል ሲሉ የአለም አቀፍ ግንኙነት ተመራማሪ አቶ እያሱ ሃ/ሚካኤል ገልጸዋል።
ዘመኑ የዲፕሎማሲ የበላይነት የሚወደስበት በመሆኑ በኢትዮ-ኤርትራ አሁናዊ ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያ በብልጠት የኤርትራን ትንኮሳ ማጋለጥ ይገባታል በማለትም ጉዳዩ ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት የሚሻ ስለመሆኑ የአለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ በኩል በሌሎች ሀገራት ምላሽ ልክ ከመመልስ ይልቅ በሰከነ የዲፕሎማሲ ስራ ውስጥ ጥቅምን አስጠብቆ ማስቀጠል ይገባል ሲሉ ሌላኛው የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ተንታኝ እና የፖለቲካ ሳይንስ መምህር አቶ ዳንኤል ወርቁ ለመናኸሪያ ሬዲዮ ሙያዊ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የሀገር ጥቅምን የሚያስከብር አካሄድ ውስጥ ለመግባት ጠብ አጫሪ ሀገራትን በትኩረት መመልከት ያስፈልጋል በማለትም በሌሎች አጀንዳ ባለመመራት በራስ መንገድ የማሸነፊያ ዲፕሎማሲ አካሄድን መቅረጽ የኢትዮጵያ ሃላፊነት መሆን አለበትም ሲሉ አቶ ዳንኤል አጽኖት ሰጥተዉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የሀገራቱን ወቅታዊ አቋም በመመልከት ዲፕሎማሲያዊ የበላይነት ብቻ በመውሰድ ጠብ አጫሪዎችን ማሸነፍ እንደምትችልም አመላክተዋል፡፡
በሁለቱም ሀገራት መካከል የከፋ ውጥረት እንዳይከሰት የሰላም አማራጮች መቅደም እንዳለባቸው በባለሙያዎቹ ተገልጿል።
ምላሽ ይስጡ