ሰሞኑን የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ጉባዔ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሦስት ዓመት የስራ አፈፃፀምን ገምግሞ የስራ ዘመኑን ለተጨማሪ 1 ዓመት ማራዘሙ ይታወቃል።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ ኮምሽኑ ባለፉት ጊዜያት በ10 ክልሎች እና ሁለቱ ከተማ መስተዳድሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ መስራቱን አስታውቀዋል፡፡
በትግራይ እና በአማራ ክልል በጸጥታ ችግር እና አስቻይ ሁኔታ ባለመኖሩ የአጀንዳ ማሰብሰብም ሆነ የተወካዮች መረጣ እንዳልተካሄደ ተናግረዋል፡፡
ስለ ኮሚሽኑ ምንነት በሚገባ አለማወቅ፤ የተዛባ አመለካከት መያዝ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሳትፎ ሁኔታ የተሟላ አለመሆን፣ በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ አካላቶችን ለማሳተፍ አስቻይ ሁኔታዎች አለመፈጠራቸው እና ሌሎችም ኮሚሽኑ በስራ ዘመኑ ያጋጠሙት ችግሮች መሆናቸውን ዋና ኮምሽነሩ አስረድተዋል።
በተሰጠው ተጨማሪ የ1 ዓመት ጊዜ በአማራና ትግራይ ክልል እንዲሁም በፌደራል እና በዲያስፖራ የተሳታፊ ልየታ እና የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ እንደሚሰራ ፕሮፌሰር መስፍን አስታውቀዋል፡፡
በተጨማሪም የምክክር ጉባዔ ተሳታፊዎችን የማሳወቅ፤ አጀንዳዎችን መቅረፅ እና ይፋ ማድረግ ተጠባቂ ስራዎች መሆናቸውን ዋና ኮምሽነሩ ገልጸዋል።
አገራዊ የምክክር ኮምሽኑ በ3 ዓመት የስራ ዘመን ቆይታው ከትግራይ እና አማራ ክልል ውጪ በሌሎች አከባቢዎች አጀንዳ የማሰባሰብ ስራውን ማጠናቀቁ ይታወቃል፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች የሚስተዋሉ የሰላም እጦት ችግሮች ለስራው እንቅፋት እንደሆነበት ነው የሚገልጸው፡፡
ምላሽ ይስጡ