በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ጉባዔ ላይ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የ3 ዓመት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት በተደረገበት ጊዜ የምክር ቤቱ አባላት ኮሚሽኑ ጊዜውን በአግባቡ አልተጠቀመም ሲሉ ተችተዋል፡፡
ኮሚሽኑ ባለፉት 3 አመታት በሃገር አቀፍ ደረጃ ያላግባቡ ችግሮችን በግልፅ ያልለየ መሆኑን አንስተው፤ እስካሁንም ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ዘልቆ አለመግባቱ በመንግስት በኩል አስቻይ ሁኔታ እንዳልተፈጠረለት የሚያሳይ ነው ሲሉ አባላቱ ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽኑ እስካሁን በሰራው ስራ የአካታችንነት ጥያቄንም የሚያስነሳ መሆኑን አባላቱ ገልጸው፤ በተሰጠው ጊዜ መስራት የሚችላቸውን ስራዎችን እንዳልሰራና የተሰጠው ተጨማሪ የአንድ አመት ጊዜም ለቀሪ ስራዎች በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽኑ ባለፉት አመታት የተፈጠሩ አለመግባባቶችን ብቻ ሳይሆን ለ60 ዓመታት ያክል ያልተፈቱ እና በአሁኑ ጊዜ ስር የሰደዱ ችግሮችን ጨምሮ ከተቋቋመበት ጊዜ ወዲህም አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በመቋቋም ተልዕኮውን በአግባቡ እየተወጣ እንዳለ በምክር ቤቱ የመንግስት ዋና ተጠሪ ዶክተር ተስፋዬ በልጂጌ ተናግረዋል፡፡
የኮሚሽኑ የምክክር ሂደት አሳታፊ እና አካታች መሆኑን ያከናወናቸው ተግባራት ማሳያ እንደሆኑም ዶክተር ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽኑ በተጨመረለት የ1 አመት ጊዜ በአማራና ትግራይ ክልሎች አስቻይ የሚባል ስራን በመስራት ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ ውጤቱን ሊያሳይ እንደሚገባ አባላቱ አንስተው ለታጣቂ ሃይሎች ግልፅ የሆነ ጥሪ በማድረግ አጀንዳዎችን ሊቀበል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የጀመራቸውን ሀገራዊ ስራዎች እንዲያጠናቅቅ የተፈቀደለት የ1 ዓመት ተጨማሪ የስራ ዘመን በ3 ተቃውሞ፤ በአብላጫ ድምፅ ጸድቋል፡፡
ምላሽ ይስጡ