በወርሃ የካቲት 1966 ዓ/ም በተቀሰቀሰው የኢትዮጵያ አብዮት ወቅት ከተነሱ ዋነኛ ጥያቄዎች አንዱ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንደሆነ ይታወቃል። ይህንኑ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በኢትዮጵያ ህገ-መንግስት ከመደንገግ ጀምሮ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውም የሚታወቅ ነው፡፡
የፌደራሊዝም እና የህግ ባለሙያ ዶ/ር ሃይለእየሱስ ታዬ በኢትዮጵያ ያለው ብዘሃነት በአግባቡ እና በትክክል ባለመስተናገዱ ለበርካታ ውዝግቦች መነሻ ሆኗል ብለዋል፡፡
በ1966 ዓ/ም ከተነሱ ዋነኛ ጥያቄዎች አንዱ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት መሆኑን አስታውሰው፤ አሁን ላይ ጥያቄው በህገ መንግስቱ ክልሎች እራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ የሚደነግግ አንቀጽ በመኖሩ በወቅቱ ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የተሰራ ስራ ቢኖርም፤ ጥያቄው ሙሉ በሙሉ ምላሽ አላገኘም ብለዋል፡፡
የህዝብን የመብት ጥያቄ መመለስ ቀላል አለመሆኑን የሚገልጹት ባለሙያ፤ በየጊዜው ህዝቡ የተለያዩ ጥያቄዎችን ይፈጥራል ያነሳል በመሆኑም ለሁሉም ምላሽ ሰጥቶ መጨረስ አይቻልም ነው ያሉት፡፡
በዚህም የተለያዩ ግጭቶች እንደሚነሱ አመላክተው፤ በየጊዜው በሚነሱ ጥያቄዎች ላይ ጥናት በማድረግ ሚዛናዊ ምላሽ መስጠት ይገባል ብለዋል፡፡
እንደሃገር ካለፈው ታሪክ በመማር ልዩነት እና ጥያቄዎችን በሰላማዊ መልኩ በንግግር መፍታት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
ምንም እንኳን በህገ-መንግስቱ የተደነገጉ ህገ-መንግስታዊ መብቶች ቢኖሩም አሁንም ድረስ የመሬትና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች ሙሉ በሙሉ አልተመለሱም የሚሉት የስነ አመራር እና የፖለቲካ መምህሩ አቶ ጌትዬ ትርፌ ናቸው፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ከሚመለከተው አካል ባለፈ ህዝቡም የራሱን ህጋዊ መብት የማስከበርና መብቱን ጠንቅቆ የማወቅ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡
ያሉብንን የጋራ ችግሮች በጋራ ለመፍታት ብሎም ለጸብ የሚጋበዙ የህግ ጉዳዮችንም ለማሻሻል በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አመላክተዋል።
እንደሃገር ያሉብንን ችግሮች ለመፍታትና በየጊዜው የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ህዝቡ የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ ባለሙያዎቹ አመላክተዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ