ኢትዮ ቴሌኮም ከጅማ ከተማ አስተዳደር ጋር በከተማዋ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያደርግ የስማርት ሲቲ “ስማርት ጅማ” ፕሮጀክትን ለመተግበር የሚያስችል ስትራቴጂያዊ ስምምነት ማድረጉን አስታውቋል፡፡
ፕሮጀክቱ ከተማዋን በሁለገብ ዲጂታል ሶሉሽኖች ለማዘመን ያለመ ሲሆን፣ የክላውድ መሰረተ ልማትን፣ የጥሪ ማዕከልን፣ ጠንካራ የመረጃ ማዕከልን፣ እጅግ ከፍተኛ ፍጥነትና ጥራት ያለው ኢንተርኔትን፣ የላቀ የሲሲቲቪ ደህንነት ካሜራ ሲስተምን፣ የኦፕቲካል ፋይበር እንዲሁም ሌሎች የዲጂታል መሰረተ ልማቶችን ያካትታል።
የዲጂታል መሰረተ ልማቱ የማዘጋጃ ቤት አገልግሎቶችን ጨምሮ በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና፣ በትራንስፖርት እና ከግብር አሰባሰብ ጋር ተያይዞ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማዘመን እንዲሁም አስተማማኝ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ከተማን ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ከመሆኑም ባሻገር እጅግ ቀልጣፋ አገልግሎት አሰጣጥን ዕውን እንዲሆን እና አጠቃላይ የከተማ ነዋሪዎች የአናኗር ደረጃ ከፍ እንዲል ያግዛል ተብሏል።
በተለይም ውቢቷን ጅማ ለቱሪዝም ቀዳሚ መዳረሻነት፣ ለኮንፈረንስ፣ ለኢንዱስትሪ እና ለተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ተመራጭ እንድትሆን የሚያስችላትን አቅም በማጎልበት ተወዳዳሪነቷን የሚያሳድግ ሲሆን፣ ይህም የንግድ እንቅስቃሴን በማነቃቃት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ያሳድጋል ተብሏል።
ኩባንያው ቀደም ሲል የስማርት ሲቲ ፕሮጀክት ስምምነት ባደረገባቸው ከተሞች፣ በአዲስ አበባ (ሲቲኔት)፣ አዳማ፣ ሸገር ሲቲ፣ ሐረር፣ ደሴ፣ ኮምቦልቻ እና ባህር ዳር የመጀመሪያውን ምዕራፍ በተሳካ ሁኔታ የተገበረ ሲሆን በጅግጅጋ ከተማ ደግሞ በትግበራ ሂደት ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
ምላሽ ይስጡ