ኢትዮጵያ በግጭት አካባቢ ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች ጥበቃ እንዲደረግ የሚያዘውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድንጋጌ እንድትቀበል ግፊት እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል።
የመንግስታቱ ድርጅት የትምህርት ቤቶች ደህንነት ማስጠበቂያ አዋጅ የወጣው ከአምስት አመት በፊት እ.አ.አ አቆጣጠር 2019 ላይ ነበር በማለት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያም ድንጋጌውን እንድትቀበል ማህበሩ ሲወተውት መቆየቱን የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዝደንት ዶ/ር ዮሃንስ በንቲ ለጣቢያችን ገልጸዋል።
ላለፉት አምስትና ስድስት አመታት እንደ ሀገር ከነበረው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ድንጋጌውን እንድንቀበል ለማድረግ ጥያቄውን ማንሳት ከመቼውም ጊዜ በላይ ተገቢ ሆኖ ቆይቶ ነበር ሲሉ የማህበሩ ፕሬዝደንት ተናግረዋል።
ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ዘርፉን ለሚመለከተው የመንግስት አካል ሲያቀርቡ መቆየታቸውንም በመጥቀስ አሁንም ምላሽ ባለማግኘቱና በግጭት አካባቢ ያሉ ትምህርት ቤቶች ደህንነት ባልተጠበቀ ቁጥር የመምህራንም ሆነ በጥቅሉ የትምህርት ዘርፉ ደህንነት አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ይታወቃል ሲሉም ዶ/ር ዮሃንስ በንቲ ገልጸዋል።
በመሆኑም ምላሽ እስኪያገኙ ድረስ ኢትዮጵያ ድንጋጌውን እንድትቀበልና ትምህርት ቤቶች ጥበቃ እንዲደረግላቸው ለማድረግ እንደሚሰሩ ነው ዶ/ር ዮሃንስ በአጽንኦት የተናገሩት።
ከበርካታ ጠቃሚ አለም አቀፍ ድንጋጌዎች መካከል አንዱ በቅርብ አመታት ውስጥ የጸደቀው የመንግስታቱ ድርጅት የትምህርት ቤቶች ደህንነት ማስጠበቂያ አዋጅ መሆኑን በመጥቀስ በተለይ ካለንበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ይህንን ድንጋጌ እንደ ሀገር መቀበልና መተግበር አስፈላጊ ስለመሆኑ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አስታውቋል።
ምላሽ ይስጡ