በትግራይ ክልል ከሳምንታት በፊት የተቋቋመው ጊዜያዊ አማካሪ ካውንስል መፍረሱን እና እሱን የሚተካ ጊዜያዊ ምክር ቤት መቋቋሙ ተገልጿል፡፡ ከ2 ሳምንታት በፊት ተቋቁሞ የነበረው አማካሪ ካውንስል አካታችነቱ ላይ ጥያቄ ሲነሳበት እንደነበረ ይታወሳል፡፡
ጊዜያዊ ምክር ቤቱ ሲቋቋም የተለያዩ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን የገለጹት የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራር አቶ ጣዕመ አረዶም፤ ከዚህ ቀደም ለአስፈፃሚ አካላት ምክረ ሃሳብ እና ሪፖርት ያቀርባል የሚለው ከዚህም በተጨማሪ በስራው ላይ የሚገኙ አስፈፃሚ አካላት ብቁ ሆነው ካልተገኙ ወይም ስራቸውን በአግባቡ ማከናወን ካልቻሉ እርምጃ የመውሰድ እና ውሳኔ ማሳለፍ የሚችል ሆኖ መሻሻሉን አብራርተዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ የስራ ዘመኑ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ቆይታ እስኪጠናቀቅ መሆኑን በማንሳት አሁን ላይ ምክር ቤቱ የተለያዩ ኮሚቴዎችን በማዋቀር ተቋማትን ኦዲት የማድረግ፣ በህገ-ወጥ መልኩ ወርቅ የሚያወጡ እና ሌሎችንም የማጣራት ስራ መጀመሩን አንስተዋል፡፡
ጊዜያዊ ምክር ቤቱ መቋቋሙ ከሳምንታት በፊት ተቋቁሞ በነበረው አማካሪ ካውንስል ሲነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን እና የአካታችነት ጥያቄ የሚፈታ ነው ሲሉ የገለፁት የትግራይ ሲቪል ማህበራት ህብረት ፕሮግራም ስራ አስኪያጅ አቶ በሪሁ ገብረ መድህን ናቸው። ምክር ቤቱ ውሳኔ ማሳለፍ የሚችል እንዲሁም ሁሉንም አካላት ያሳተፈ በመሆኑ ልክ እንደ አማካሪ ካውንስሉ የሚፈርስ ሳይሆን ቀጣይነት የሚኖረው ነው ብለው እንደሚያምኑ ገልፀዋል፡፡
አማካሪ ካውንስሉ የትግራይን ህዝብ ጥያቄ ያማከለ አለመሆኑ እና አካታችነቱ ላይ ቅሬታ የነበረበት በመሆኑ ያልተሳተፈው የሳልሳይ ወያኔ ትግራይ ፓርቲ አሁን ላይም ጊዜያዊ ምክር ቤቱ ሲቋቋም ጥሪ ቢቀርብላቸውም፤ እንዳልተሳተፉ የሳልሳይ ወያኔ ትግራይ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ብርሃነ አጽብሃ ገልጸዋል። ነገር ግን ምክር ቤቱ ያወጣቸው ደንቦች መሻሻላቸውን ማረጋገጥ እንደሚፈልጉ እና ይህንንም ጥያቄ በደብዳቤም ጭምር መጠየቃቸውን በመግለፅ የተሻሻለው ደንብ እስኪላክላቸው እየጠበቁ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አማካሪ ካውንስል በ53 የድጋፍ ድምፅ፣ በ1 ተቃውሞ እና 2 ድምጸ ተአቅቦ ፈርሶ ጊዜያዊ ምክር ቤቱ በይፋ ተቋቁሞ ስራ መጀመሩ ይታወቃል፡፡
ምላሽ ይስጡ