ኤ.ኤች.ኤፍ ኢትዮጵያ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭትን ለመቆጣጠር እየሰራ እንዳለ ገልጻል፡፡ ተቋሙ በየትምህርት ቤቶች እና ከትምህርት ቤት ውጪ አፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ከኤች አይ ቪ እንዲጠበቁ የምርመራ ግብዓቶችን በማሟላት እና የባለሙያዎችን አቅም በማጎልበት እየሰራ መሆኑን ነው የገለጸው፡፡
የጤና ተቋማት በግብዓት እና ባለሙያ እጥረት ምክንያት የሚሰጡት የኤች አይ ቪ ኤድስ ምርመራ እና የህክምና አገልግሎት እንዳይቆረጥባቸው ድጋፍ እንደሚያደርግ የገለጹት የኤ.ኤች.ኤፍ ኢትዮጵያ የኤች አይ ቪ መከላከል እና ምርመራ ዳይሬክተር አቶ ቶሎሳ ኦላና ናቸው።
በኦሮሚያ፤ አማራ፤ ሲዳማ ክልል እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሚገኙ 19 የጤና ተቋማት እንዲሁም 61 ሺህ ለሚጠጉ ታማሚዎች የኤች አይ ቪ ምርመራ እና የህክምና ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል፡፡
የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል ከተለያዩ የኮንዶም አስመጪዎች ምርቱን በመግዛት ቢያከፋፍሉም በቂ ባለመሆኑ ካለፉት 2 ዓመታት ጀምሮ ኤ.ኤች.ኤፍ 3 ሚሊየን የሚጠጋ የራሱን ብራንድ ኮንዶም ከማሌዢያ በመግዛት ተቋሙ ለሚደግፋቸው ክልሎች ማከፋፈሉን አስታውቀዋል፡፡
በመንግስት በኩል 55 ሚሊየን ኮንዶም ድጋፍ እንደሚደረግ የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ በአጠቃላይ የሚያስፈልገው መጠን ግን 270 ሚሊየን ኮንዶም ነው ብለዋል፡፡
በቅርቡ የUSAID ድጋፍ መቋረጥን ተከትሎ አቅርቦት ላይ እጥረት ሊኖር እንደሚችል ያስታወቁት ኃላፊው፤ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶችም ምርቱን በብዛት ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት በታክስ ጫና ምንክያት አቅማቸው መዳከሙን ነው የተናገሩት።
ኤ.ኤች.ኤፍ ኢትዮጵያ፣ ጤና ሚንስቴር እና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በጋራ በመሆን በኢትዮጵያ ለ10ኛ ጊዜ የሚከበረውን የኮንዶም ቀን “ይጠቀሙ” በሚል መሪ ቃል አክብረዋል። ቀኑን ከፖሊስ ኮሚሽን ጋር ማክበር ያስፈለገበት ምክንያት ሰራዊቱ በስራ ምክንያት ወደ ተለያዩ አከባቢዎች ሲዘዋወር በሔደበት ሁሉ ግንዛቤ እንዲፈጥር እና እንዲፈጠርለት በማሰብ መሆኑን የኤ.ኤች.ኤፍ ኢትዮጵያ የኤች.አይ.ቪ መከላከልና ምርመራ ዳይሬክተር አቶ ቶሎሳ ኦላና አስታውቀዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ