በአዲስ አበባ ከተማ ሲካሄድ የቆየው 38ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ እና 46ኛው የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ በስኬት መጠናቀቁን የፀጥታና ደኅንነት ጥምር ኃይል አስታውቋል፡፡
የፀጥታና ደኅንነት ጥምር-ኃይሉ ለመገናኛ ብዙኃን በላከው ጋዜጣዊ መግለጫ የአዲስ አበባ ከተማን ሰላምና ደህንነት የበለጠ በማጠናከር የኅብረተሰቡ እንቅስቃሴ ሳይገታ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ የትራፊክ ፍሰቱን የተሳለጠ በማድረግ በቅንጅት በመሥራቱ ጉባኤው በስኬት መጠናቀቁን ገልጿል።
በጉባኤው ላይ ለመሳተፍ የመጡ እንግዶች በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ እጀባና አስተማማኝ ጥበቃ ማድረጉን ጥምር ኃይሉ በመግለጫው አመላክቷል።
ፀጥታን የማስከበር ተግባሩ አፍሪካን ሊያኮራ የሚችል እና ሀገራችን የአፍሪካ ኅብረትን ለማጠናከር ያላትን ሚና እና ቁርጠኝነትን አጉልቶ ያሳየ እንደነበርም ጥምር-ኃይሉ በመግለጫው አንስቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በከፍተኛ ደረጃ ተባብረው በመሥራት ላደረጉት ቀና ትብብር እንዲሁም የፀጥታና ደህንነት ጥምር-ኃይል አመራርና አባላት በጥብቅ ዲሲፕሊን የተሰጣቸውን ተልዕኮ በስኬት በመወጣታቸው የፀጥታና ደኅንነት ጥምር-ኃይል በመግለጫው ላቅ ያለ ምስጋና አቅርቧል፡፡
ምላሽ ይስጡ