በጋምቤላ ክልል ኑዌር ብሔረሰብ ዞን አራት ወረዳዎች የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታ ተከሰተ
🔰በአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታ የዘጠኝ ሰው ሕይወት ሲያልፍ 136 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው ተገልጿል
የካቲት 10 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)በጋምቤላ ክልል ኑዌር ብሔረሰብ ዞን በአኮቦ፣ ዋንቱዋ፣ ማኩዌይ እና ላሬ ወረዳዎች የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታ ተከስቶ የዘጠኝ ሰው ሕይወት ሲያልፍ 136 ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አቤል አሰፋ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ከዚህ ቀደም በክልሉ አጎራባች ከሆነው አገር ደቡብ ሱዳን በሽታው ተከስቶ እንደነበር አስታውሰዋል።
በመሆኑም በጋምቤላ ክልል በኑዌር ብሔረሰብ ዞን በአራት ወረዳዎች ማለትም በአኮቦ፣ በዋንቱዋ፣ በማኩዌይ እና በላሬ ወረዳዎች የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታ መከሰቱን አስታውቀዋል።
በበሽታው ከተያዙት 136 ሰዎች መካከል የዘጠኝ ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 31 ሰዎች በህክምና ላይ ሲገኙ 96 ሰዎች ደግሞ ከበሽታው ማገገማቸውን ዶክተር አቤል ተናግረዋል።
በሽታውን በተከሰተባቸው አራት ወረዳዎች ቡድን በመላክ መድሃኒቶችና የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶችን ማድረስ መቻሉን ጠቁመዋል።
በሽታው ወደሌሎች አካባቢዎች እንዳይስፋፋም ሕብረተሰቡ አካባቢውን እንዲያጸዳ፤ ንጽህናውን እንዲጠብቅም አሳስበዋል።
ለማንኛውም አገልግሎት የሚውልን ከቧንቧ፣ ከጉድጓድ፣ ከምንጭ፣ ከወንዝ እና ከመሳሰሉት የተቀዳ ውሃን በውሃ ማከሚያ መድሐኒቶች በማከም ወይም በማፍላት መጠቀም እንደሚገባም አስታውቀዋል።
ምግብን ከማዘጋጀት፣ ከማቅረብ እና ከመመገብ በፊት ከመጸዳጃ ቤት መልስ እና ሕጻናትን ካጸዳዱ በኋላ እጅን በሳሙና መታጠብ እንደሚገባም ዶክተር አቤል አስታውሰዋል።
ምላሽ ይስጡ