የካቲት ወር የድል በዓላት የሚበዙበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በርካታ ኢትዮጲያዊያን ዓርበኞች የሚዘከሩበት እና ገድላቸው የሚነገርበት መሆኑ የሚታወቅ ነው ። ድል የተደረገባቸውን ቀናት እየቆጠሩ ከማክበር ባለፈ በቋሚነት አሁን ላይ በሃገሪቷ በህይወት ያሉ ዓርበኞች የመደገፍ ፣ የማደራጀት ብሎም ያላቸውን የታሪክ እውቀት ሰንዶ ከማስቀመጥ አንጻር እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በተመለከተ መናኸሪያ ሬዲዮ የአርበኞች ማህበርን አነጋግሯል ።
የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፈን እንደገለጹት ማህበሩ በአዲስ አበባና በክልሎችም ቢሮዎች አሉት በስሩም ታሪኮችንና አርበኞቹን በማደራጀት የተለያዩ ታሪካዊ ሰነዶችን የማሰባሰብ ሰራዎችን እየሰራ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በመንግስት በኩል የተለያዩ ድጋፎች የሚደረግልን ቢሆንም አሁንም የተስፋፋና የተደራጀ ስራ ለመስራት የበጀት እጥረት አለብን ሲሉ የሚገልጹት ፕሬዝዳንቱ፤አዲሱ ትውልድ የቀደመ ታሪኩን እንዲያውቅና የራሱንም የታሪክ አሻራ ሰርቶ እንዲያልፍ በየጊዜው ከ10-15 የሚደርሱ ትምህርት ቤቶች በመገኘት የማነቃቃት ስራዎችን እየሰሩ ስለመሆናቸዉ አስረድተዋል፡፡
አሁን ላይ ማህበሩ እየሰራባቸው ካሉ ታሪክን ሰንዶ የማስቀመጥ ስራዎች ላይ ከበጀት እጥረቱ በተጨማሪ የተለያዩ ሃገራዊ ታሪኮችን የሚያውቁ ዓርበኞች የሚያውቁትን ታሪክ ለመናገር ፈቃደኛ ባለመሆናቸዉ የታሪክ ከፍተትን የሚፈጥር ነው ሲሉ አመላክተዋል ።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ዓርበኞቹን በየቤታቸው የመጠየቅና የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶችን በነጻ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ሲሉ ገልጸው ፤ በከተማ አስረዳደሩ በኩልም ቤት የሌላቸው ቤት እንዲሰጣቸዉ ፤ነጻ ትራንስፖርት እንዲያገኙ የማደረግ በርካታ ስራዎችን እየሰሩ መሆኑንም አስረድተዋል ።
ምላሽ ይስጡ