የካቲት 5 ቀን 2017 ዓ.ም በጅማ ዞን ጌራ ወረዳ ውስጥ በኢንቨስትመንት ተሰማርተው ይሰሩ በነበሩት በአቶ ዛኪር አባ ኦሊ ላይ አስደንጋጭ ግድያ ተፈፅሟል።
የአከባቢው ነዋሪም ግድያውን በማውገዝ መንግስት ወንጀለኞችን በአፋጣኝ ለህግ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል በዚህ ምክንያት ተደናግጠው አካባቢውን በመልቀቅ የተወሰኑ ሰዎች ወደ ሌላ አከባቢ ሸሽተዋል።
መንግስት ጉዳዩ ተፈፀመ ከተባለበት ሰዓት አንስቶ ከህዝቡ ጋር በመሆን ተጠርጣሪዎቹን በመያዝ ለህግ የማቅረብ ስራን እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ተደናግጠው አከባቢውን ለቀው ወደ ሌላ ቦታ ሸሽተው የነበሩ ነዋሪዎችንም በመመለስ ላይ እንደሚገኝ ተመላክቷል።
ይሁን እንጂ አንዳንድ ተቋማትና ግለሰቦች ጉዳዩን የብሔርና የሀይማኖት መልክ እንዳለው አድርገው በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ ያስታወቀው መግለጫው፤ ይህ የሚያሳያው ተቋማቱ ድብቅ ተልዕኮና በጉዳዮ ላይ እጃቸው እንዳለበት የሚያመላክት ነው ብሏል።
በተጨማሪም ተቋማቱ ማህበረሰቡ ለረጅም አመታት ተጋምዶ የገነባውን ማህበራዊ ቁርኝት በመበጠስ የብሔርና የሀይማኖት ግጭት ለመፍጠር እየሰሩ መሆናቸውን አመላክቷል።
መንግስት ከህዝቡ ጋር በመሆን የጀመረውን ወንጀለኞችን በማደን ለህግ የማቅረብ ስራን አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ያለው መግለጫው ፣ ጉዳዩን መነሻ በማድረግ ድብቅ አጀንዳን ለማሳካት በመጣር ላይ የሚገኙ ሁሉ ከድርግታቸው እንዲቆጠቡ መንግስት ማሳሰብ ይወዳል ሲል የኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ በማህበራዊ ድህረ ገፁ ባወጣው መግለጫው አስታውቋል።
ምላሽ ይስጡ