አሜሪካ ግብጽ የጋዛ ነዋሪዎችን ተቀብላ እንድታሠፍር ለማግባባት የሕዳሴ ግድብን አጀንዳ እንደ መሳሪያ ልትጠቀምበት እንደምትችል፣ ይህም በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ስጋት የሚደቅን መሆኑ እየተገለጸ ነው።
ከዚህ ስጋት ለመውጣት ቀሪ የግድቡን ስራ በፍጥነት ማጠናቀቅ እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት አስታውቋል።
የግድቡን ሃይል የማመንጨት ስራ በተቀላጠፈ መልኩ ማስኬድ ጊዜ የማይሰጠው የቤት ስራ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባም ኢንስቲትዩቱ ለጣቢያችን ገልጿል።
የሕዳሴ ግድብ ውዝግብን ለመፍታት አሜሪካ ገንቢ ሚና እንድትጫወት ከተፈለገ፣ ግብጽ የጋዛ ነዋሪዎችን ተቀብላ ማስፈር እንዳለባት የአሜሪካ ባለሥልጣናት ከግብጽ አቻዎቻቸው ጋር መምከራቸው በቀጥታ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ያነጣጠረ በመሆኑ ትኩረት የሚሻው ጉዳይ ነው ብሏል ተቋሙ።
በኢኒስቲትዩት የአሜሪካና አውሮፓ ጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት ተመራማሪ አቶ ታሪኩ አብርሃ ግብፅ የጋዛ ስደተኞችን በመቀበል ለትራምፕ አስተዳደር ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ከወሰነች ለኢትዮጵያ አደጋን ሊደቅን ይችላል ሲሉም ተናግረዋል።
ምንም እንኳን ውሳኔው በግብፅ የሚቃኝ ቢሆንም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት እና ተመድን በማነጋገር አሉታዊ ተፅዕኖውን ለመቋቋም ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ መስራት አለባት ብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቀደመው የሥልጣን ዘመናቸው፣የግድቡን ውዝግብ ለመፍታት ያቀረቡትን አስገዳጅ የስምምነት ሰነድ ኢትዮጵያ ውድቅ ማድረጓ ይታወሳል።
ምላሽ ይስጡ