አካል ጉዳተኞች ምርት እና አገልግሎቶቻቸውን በማስተዋወቅ እና ለገበያ በማቅረብ ሒደት የሚገጠሟቸውን ችግሮች መቅረፍ የሚስያችል የዲጂታል ስልጠና ስርዓተ ትምህርት ተቀርጾ በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ሊሰጥ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታዉቋል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አካል ጉዳተኞች የሚገጥማቸውን ፈተናዎች በመገንዘብ፣ ክፍተቶችን ለማጥበብ እና ለማብቃት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ እንዳለ አስታውቋል። የዲጂታል ግብይት ክህሎት በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ሥርዓት ተካቶ እንዲማሩበትና ተጠቃሚ እንዲሆኑ በስርዓተ ትምህርት ደረጃ ተቀርጾ በተቋማቱ ቀጣይነት ባለው መልኩ ስልጠናዎች እንዲሰጡ ለማድረግ የዝግጅት ምዕራፍ እየተጠናቀቀ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ሥልጠናውን የሚወስዱት በዲጂታል ግብይት አስፈላጊው እውቀትና ተግባራዊ ክህሎት እንዲኖራቸው በማሰብ ስርዓተ ትምህርቱ መዘጋጀቱን የገለጹት በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የገበያ ጥናትና ትስስር ዴስክ ተወካይ ወይዘሮ ሶስና አድማሱ ናቸው።
ሥርዓተ ትምህርቱ ከዲጂታል ግብይት እና የስራ ፍለጋ ማሻሻያ ጀምሮ፣ እስከ ኢ-ኮሜርስ እና የመስመር ላይ የሽያጭ ስትራቴጂዎች ድረስ የተለያዩ ገጽታዎች እንደሚኖረው ገልጸዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም በዝርዝር የተዘጋጁ የሥልጠና ሰነዶችን እና ግብዓቶችን አዘጋጅቶ ወደ ትግበራ ለመግት ዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በቀጣይ የተዘጋጁ ሰነዶች በመላ አገሪቱ ለሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ተሰራጭው፣ የሙያ ተቋማትም በትምህርት ስርዓታቸው እንዲያካትቱ ይደረጋል ብለዋል፡፡ ሥራ ፈላጊ አካል ጉዳተኞችን በዲጂታል ዓለም ውስጥ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን እንዲያገኙ ማብቃት፣ እነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ የዲጂታል ግብይት ክህሎት በማግኘት ምርቶቻቸውንና አገልግሎቶቻቸውን በመስመር ላይ በማስተዋወቅና በመሸጥ የቦታ እና የጊዜ እንቅፋቶችን ሰብረው፣ ተደራሽ እንዲሆኑ እንደሚያስችላቸውም ጠቁመዋል፡፡
ለአካል ጉዳተኞች የተዘጋጁ የዲጂታል ስልጠና ስርዓተ ትምህርት ገቢያቸውን እና የኢኮኖሚ ነፃነታቸውን ከማሳደግ በተጨማሪ ዓለም አቀፋዊ ገበያዎችን እንዲጠቀሙ ያስችላቸዋል የተባለ ሲሆን ለሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገትም አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዳለው ተልጿል፡፡
ምላሽ ይስጡ