የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 18ኛ መደበኛ ስብሰባውን በትላንትናው እለት ባካሄደበት ወቅት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የጎዳና ተዳዳሪዎችን ሙሉ መረጃ የማስመዝገብ ግዴታ እንዳለበት የሲቪል እና የቤተሰብ ምዝገባ ስርዓት አዋጅን ሲያጸድቅ አስታውቋል።
የጎዳና ተዳዳሪዎችን የወሳኝ ኩነት መረጃዎችና የቤተሰብ ምዝገባ ሃላፊነትን ከዚህ ቀደም በጥቅሉ የሚመለከተው የመንግስት አካል ይመዘግባል ተብሎ እንደተቀመጠ ተገልጿል፡፡
አሁን ላይ ተሻሽሎ እንደ አዲስ በወጣው አዋጅ ኃላፊነቱ ለሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደተሰጠው የምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ነጎ ገልጸዋል።
የሚመለከተው የመንግስት አካል ተብሎ ኃላፊነቱ ክፍት መደረጉ ይሻላል ሲሉ ከምክር ቤቱ አባላት በጉዳዩ ላይ አስተያየት የተሰጠበት ሲሆን ለዚህም እንደ ምክንያት የተጠቀሰው ተለዋዋጭ የሆነው የመንግስት አደረጃጀትና አቀራረብ ነው።
አዋጁ የጎዳና ላይ ህጻናት እያለ መጥቀሱ ተገቢ አይደለም፤ ጎዳና ላይ የሚኖሩት ህጻናት ብቻ ባለመሆናቸው ሌሎችንም አካላት ማካተት እንደሚገባም ጠይቀዋል። በተጨማሪም በወሳኝ ኩነትና ቤተሰብ ምዝገባ ወቅት ብሄርና ሃይማኖት ተጠይቆ መመዝገቡ ተገቢ አይደለም በሚልም በአባላቱ ጥያቄ ተነስቷል፡፡
የምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ነጎ በበኩላቸው የሚመለከተው የመንግስት አካል ከሚል ግልጽ ያልሆነ አሰራር መውጣት አለብን፤ ተጠያቂነትን ለማስፈን በግልጽ ባለቤቱ መለየት አለበት ብለዋል፡፡
በወሳኝ ኩነትም ሆነ በቤተሰብ ምዝገባ ወቅት የሀገር ውስጥ ዜጋን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር ማንኛውም የውጭ ዜጋ እንደሚካተት የሲቪል እና የቤተሰብ ምዝገባ ስርዓት አዋጅ ይደነግጋል።
ምላሽ ይስጡ