ኢትዮጵያ የጥናት እና ምርምር ውጤቶችን በመቅዳት በአለም ቀዳማዊ ሀገር መባሏን ተቀማጭነቱን በሕንድ ሀገር ያደረገው አለም አቀፍ ሪሰርች ዎች የተሰኘ ተቋም በማህበራዊ ትስስር ገጹ መረጃውን ማጋራቱ ይታወቃል።
የመረጃውን ትክክለኝነት በተመለከተ መናኸሪያ ሬድዮ የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩትን ጠይቆል።
ኢንስቲትዩቱ ባደረገው ጥናት በኢትዮጵያ የተደረጉ ጥናትና ምርምሮች በ7 ዋና ዋና ምክንያቶች የሪፖርቱን ትክክለኛነት አረጋግጧል ሲሉ የኢንስቲትዩቱ የኮሙኒኬሽን ሀላፊ ዶክተር በለው ደምሴ ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቀዋል።
በተደረገው ጥናት በመረጃ አሰባሰብ፣ በሌላ አካል የተጻፉ ጽሑፎችን ቋንቋ ብቻ በመቀየር መጠቀም፣ የሀሰት መረጃዎችን በማካተት፣ በስነ-ምግባር ጉድለት፤ ያለፍቃድ ጥናት በማድረግ፣ በፅሁፍ ድግግሞሽ፣ በወገንተኝነት እና በባለሙያ አለማስገምገም እንዲሁም በዘፈቀደ ጥናቶችን የማውጣት ችግሮች እንደሚስተዋሉ ገልጸዋል፡፡
ጥናቶችን ከዚህ በፊት መቆጣጠር ያልተቻለው የጥናቶቹ ክፍት አለመሆን ነው የሚሉት ኃላፊው፤ በምርምር ተቋማት የሚደረጉ ጥናቶች ሙያዊ ስነ-ምግባርን መከተላቸውን፣ በሚጠበቀው ሂደት ማለፋቸውን ለመቆጣጠር የጥናቶቹ ክፍት መሆን ወሳኝ ሚና እንዳለው አመላክተዋል።
በቀጣይ ጥናቶች ሲደረጉ ለማረጋገጥ በርካታ የቴክኖሎጂ አማራጮች ጥቅም ላይ እንደሚውሉ እንዲሁም ምርምሮቹን ከሌሎች የምርምር ውጤቶች ጋር ለማመሳከር ከአለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትስስር እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
ምላሽ ይስጡ