የፌደራል የስነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ከኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበር ጋር በስራ እድል ፈጠራ ዙሪያ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን ለመቅረፍ እንዲሁም የስራ እድል ፈጠራ መረጃን ከጥራት እና ተገቢነት አንጻር ለመፈተሽ የሚያስችል ስራ ለመስራት የጋራ የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሙ ተገልጿል።
በወጣቶች ስራ እድል ፈጠራ ዘርፍ በርካታ ስራዎች ቢሰሩም ችግሮች እንዳሉ ነው የተገለጸው።
በተለይም የስራ እድል ፈጠራ ስልጠናዎች የተሟሉና የንግድ ስነ ምግባርን የተከተሉ አለመሆን፤ በዚህ ዙሪያ ያሉ መረጃዎች ከግልጽነትና ከጥራት አንጻር ክፍተቶች የሚስተዋሉባቸው በመሆኑ ለማረም እንዲቻል ከማህበሩ ጋር ስምምነት መድረጉን የሚገልጹት የፌደራል የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ ናቸው፡፡
በተለይም የስራ እድል ፈጠራ ላይ የተሰማሩ መንግስታዊም ሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በዚህ ጉዳይ የሚሰሩት ስራ ከስነ ምግባር፤ ከትክክለኛነት፤ ከዘላቂነት እና ከሙስና የጸዳ መሆኑን በመረጃ ላይ በመመስረት የመገምገም እና የስራ ፈጠራ አውዱን ጤናማ የማድረግ ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ሳሚያ አብድልቃድር በበኩላቸው ወጣት ስራ ፈጣሪዎች የፋይናንስ አቅርቦት፤ የገበያ ስርዓት እንዲሁም የስልጠና እድሎችን በተመለከተ የሚያገኙት መረጃ ከብልሹ አሰራር የጸዳ፤ ስነ ምግባርን የተላበሰ እንዲሆንና በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ከመሰል ተቋማት ጋር መስራት አስፈላጊ በመሆኑ ስምምነት መፈጸሙን ገልጸዋል።
ሙስናን ለመከላከል በሚሰራው ስራ ወጣቶች ተሳታፊ እየተደረጉ መሆኑ ተገልጻል።
ምላሽ ይስጡ