የብሄራዊ ባንክና የኢትዮጵያ ኦዲት ቦርድ አገልግሎታቸውን የጨረሱ ሰነዶች እንዲወገዱ መደረጉን የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መፅሀፍት አገልግሎት ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል፡፡
አገልግሎቱ በተሰጠው ስልጣን መሰረት የመንግስት ተቋማት 25 አመታትን ያስቆጠሩና አገልግሎት የማይሰጡ ሰነዶችን በመለየት የማስወገድ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጽሀፍት አገልግሎት የብሄራዊ ሰነድ አስወጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መኮንን ከፍያለ ተናግረዋል፡፡
ይህ ሰነድ ለማስወገድ በርካታ ባለሙያዎች መሳተፋቸውን በመግለፅ ሰነዶችን ለማስወገድ በተሰራው ስራ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰነዶች ለጥናት ምርምር እንዲውሉ ተመርጠው መቀመጣቸውን ገልፀዋል፡፡ እነዚህ የተለዩ ሰነዶች ለሀገር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው በመግለፅ በእነዚህ ተቋማት አገልግሎት የማይሰጡ ሰነዶች ስለተወገደላቸው በሚሊዬን የሚቆጠር ኪሳራን ማትረፍ ተችሏል ብለዋል፡፡
የብሄራዊ ባንክ ሰነዶች ባለሙያ አቶ ዳዲ መኮንን በበኩላቸው በባንኩ በርካታ ለአገልግሎት የማይውሉ ሰነዶች መኖራቸውን በመግለፅ አሁን ላይ ከ10 ሺ በላይ ሰነዶች በኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተ መፀሀፍት አገልግሎት በኩል እንዲወገዱ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ብሄራዊ ባንክ ከእነዚህ ሰነዶች ባሻገር ሌሎቹን ወደ መረጃ ቋት ለማስገባት ጥናት እያደረገ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጽሀፍት አገልግሎት በተሰጠው ስልጣን መሰረት አገልግሎታቸው ያበቃ ሰነዶችን በማስወገድ ሰነዱ ዳግም አገልግሎት እንዲሰጥ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ