የኢትዮጵያና ኬንያ የደኅንነትና የጸጥታ ተቋማት በሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢ በሚንቀሳቀሰው የሸኔ ታጣቂ ላይ የተቀናጀ ኦፕሬሽን ማካሄድ መጀመራቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኃን የላከው መረጃ እንዳስታወቀው፤ የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የኬንያ ብሔራዊ መረጃ አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ኑረዲን ሞሐመድ ሐጂ እንዲሁም የሁለቱ ሀገራት የመከላከያ እና የፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች ምክክር አድርገዋል።
በጋራ ባካሄዱት የጋራ መድረክ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በቀጣናዊ የጸጥታ እና ደኅንነት ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመሥራት የተፈራረሟቸውን ስምምነቶች ተግባራዊ ለማድረግ የተቀናጀ ኦፕሬሽን ማካሄድ ተጀምሯል፡፡
በሁለቱ ሀገራት ብሔራዊ ጥቅሞች ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉትን ሽብርተኝነት፣ የኮንትሮባንድ ንግድ፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች እና የመሣሪያ ዝውውርን ለመከላከል ተግባራዊ መሆን የጀመረው የተቀናጀ ኦፕሬሽን በዋናነት በእነዚህ እንቅስቃሴዎች የሚሳተፈውን የሸኔ ታጣቂ ከሁለቱ ሀገራት ድንበሮች አካባቢ ለማስወገድ የሚረዳ እንደሆነ መረጃው አመልክቷል፡፡
በዚህም መሰረት የሁለቱ ሀገራት የደኅንነትና የጸጥታ አካላት በየድንበራቸው ውስጥ በሚገኙ የቡድኑ ካምፖች ላይ የተቀናጀ ኦፕሬሽኖች እያካሄዱ ይገኛሉ፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ የኬንያ ብሔራዊ የፖሊስ አገልግሎት በበኩሉ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፤ የሸኔ ቡድን በሀገሪቱ የድንበር አካባቢ በመንቀሳቀስ ድንበር ተሻጋሪ በሆኑ ወንጀሎች ላይ ይሳተፋል፡፡
ቡድኑ በሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ፣ የሰዎችና የማዕድን ንግድ እንዲሁም የጎሳ ግጭት በመቀስቀስ በሚያደርገው እንቅስቃሴ የሀገሪቱ የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ሆኖ ቆይቷል፡፡
በዚህም የተነሳ የኅብረተሰቡን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ መጠነ ሰፊ ኦፕሬሽን መካሄድ ጀምሯል፡፡ እስካሁን በተከናወኑ ኦፕሬሽኖችም በታጣቂ ቡድኑ ላይ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ደርሷል፡፡
የተጀመረው የተቀናጀ ኦፕሬሽን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያረጋገጠው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መረጃ፤ የሸኔ ታጣቂ ቡድን የቀረበለትን የሰላም ጥሪ በመርገጥ በራሱ ላይ ጥፋት ቢያውጅም፤ አሁንም የሰላም መንገዱ ዝግ አለመሆኑን ጠቁሟል፡፡
ቀሪዎቹ የቡድኑ አባላትም የጥፋት መንገዱን በመተው የቀረበላቸውን የሰላም አማራጭ እንዲቀበሉ ጥሪ መቅረቡን አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ለመገናኛ ብዙኃን የላከው መረጃ አስታውቋል፡፡
ምላሽ ይስጡ