ጥር 26 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)በአማራ ክልል ያሉ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የጤና፣ ህግ፣ ታሪክና መሰል የትምህርት መስኮች የሚማሩ ተማሪዎችን ለተግባር ተኮር ስልጠና ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ለመውሰድ በክልሉ ያለው የጸጥታ ችግር ተግዳሮት እንደሆነባቸው በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል ሃላፊው መላኩ ጥላሁን ለጣቢያችን ገልጸዋል፡፡
የተግባር ተኮር ስልጠና በዩኒቨርሲቲው የትምህርት ካሪኩለም የተካተተ በመሆኑ አሁን ላይ የህግ ትምህርት ክፍል ተማሪዎች ራቅ ወዳለ ቦታ ሳይሄዱ በከተማው ለማሰልጠን እንደታቀደ አመላክተዋል፡፡
ነገር ግን እንደ ታሪክ እና ጤና የመሳሰሉት የትምህርት መስክ ሰልጣኞች ወደ ሌላ ክልል እና ከተማ ተንቀሳቅሰው የሚማሩት እንደመሆኑ ሰልጣኞች ከሌሎች ጋር በሚኖራቸው ውድድር ተጽዕኖ እንደሚፈጥርባቸው አክለዋል፡፡
በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ ክፍለ ዮሃንስ፣ በክልሉ ያለው የሰላም እጦት ለተግባር ተኮር ስልጠና ተግዳሮት ቢሆንም ደብረ ብርሃን ለአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት የሚገኝ በመሆኑ ከሌሎቹ በተሻለ ተማሪዎቹ የተግባር ተኮር ስልጠና ይወስዳሉ ብለዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲው ጊቢ ባለው ሆስፒታል እንደሚሰለጥኑም ነው የተናገሩት፡፡
ዩኒቨርሲቲዎቹ ለተማሪዎቹ ደህንነት ሲባል በአቅራቢያ ካሉ ከተሞች እንዲሁም የተለያዩ ተቋማት ጋር በመነጋገር የተግባር ተኮር ስልጠና እንደሚሰጡ አመላክተዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ