አመራሮቹ ለሰብአዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር የሚኖራቸው ሚና እንዲሁም የሚጣልባቸው ሃላፊነት የህዝብ አደራ በመሆኑ ከሃላፊነቱ በፊት በዘርፉ ላይ የኋላ ታሪክ ሊኖራቸው እንደሚገባ ባለሙያዎች ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቀዋል፡፡
በተለይም የውጭ ጠላቶች ዜጋን መጨቆን ከፈለጉ ከሚጠቀሟቸው ተቋማት የሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብት ላይ የሚሰሩ ተቋማት በመሆናቸው ሃገራዊ ሃላፊነት ላይ የቆዩና በዘርፉ በቂ ልምድ ያላቸው ሊሆኑ እንደሚገባ የቀድሞ ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ተናግረዋል፡፡
ከሰሞኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ17ኛው መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር መሾሙን የሚያስታውሱት አምባሳደር ጥሩነህ፤ መንግስት እና ህዝብ ከኮሚሽነሩ የሚጠብቋቸውን ሃላፊነት በአግባቡ በመወጣት የህዝብን ሰብዓዊ መብት ማስጠበቅ እንደሚገባቸው ገልፀዋል፡፡
በሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብት ላይ እንዲሰሩ የሚመረጡ ኃላፊዎች ከዚህ ቀደም የሰሯቸው ስራዎች እና የኋላ ታሪካቸው በሚገባ መጠናት እንዳለበት የሚናገሩት ደግሞ አለም አቀፍ የህግ ባለሙያው አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ ናቸው፡፡
ተመራጭ አመራሮቹ የፖለቲካ ውግንናቸው በጥብቅ ሊፈሽ እንደሚገባ የሚያነሱት ባለሙያው ለዜጎች ሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር እና የዜጎችን እንባ ማበስ እንደሚችሉ የሚታመንባቸው ሊሆኑ ይገባል ብለዋል፡፡
ገለልተኛ የዲሞክራሲ ተቋማትን የሚመሩ ሃላፊዎች የዜጎችን ሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብት ማስከበርን ማዕከል አድርገው መስራት እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡
ምላሽ ይስጡ