ጥር 22 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) ኮሚሽኑ በተሰጠው የሦስት አመት ጊዜ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራውን ማጠናቀቅ ባለመቻሉ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ጥያቄ ቢያቀርብም እስካሁን ምላሽ እንዳላገኘ ኮሚሽኑ ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ ተጨማሪም ጊዜ እንደሚያስፈልገው ለህዝብ ተወካዮች ቋሚ ኮሚቴ ማሳወቁን የሚናገሩት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ ኮሚሽኑ እስካሁን በሄደበት እርቀት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ የአጀንዳ ማሰባስብ ስራዎችን እየሰራ ቢሆንም በቂ አለመሆኑን አንስተው በተለይም ተጨማሪ ጊዜው በትግራይ እና በአማራ ክልል ያሉ አጀንዳዎችን ለማሰባሰብ እንደሚረዳው ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽኑ የሦስት አመት ጊዜው ሊጠናቀቅ የሳምንታት እድሜ ብቻ እንደቀረው የሚያነሱት ቃል አቀባዩ ግጭቶች ያሉባቸው አካባቢዎች ላይ አስቻይ ሁኔታ ባለመኖሩ የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ አለመከናወኑን ገልፀዋል፡፡
በትላንትናው እለት ጥር 21 ቀን 2017 ዓ.ም ከህዝብ ተወካዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር ውይይት መደረጉን እና ኮሚሽኑ ለቋሚ ኮሚቴው በሦስት አመት ውስጥ የተሰሩ ስራዎችንና ቀጣይ ስለሚያስፈልገው ተጨማሪ ጊዜ መወያየታቸውን ጠቁመዋል፡፡
ኮሚሽኑ በመላው ኢትዮጵያ ከ1ሺ 300 በላይ ወረዳዎችና በክልል የሚገኙ የከተማ አስተዳደሮች ተሳታፊዎችን ለመለየት አቅዶ እየሰራ ሲሆን እስካሁን በ10 ክልሎች እና 2 ከተማ መስተዳድሮች 1 ሺህ 350 ወረዳዎች አጀንዳ እንደተቀበለ የሚታወቅ ነዉ፡፡
ምላሽ ይስጡ