ጥር 22 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት አስር ቢሊዮን ብር እዳ መከፍሏን እንዲሁም በአሁን ወቅት የGDP እና የእዳ ጥምርታዋ ከአራት አመት በፊት ከነበረበት 30 በመቶ ወደ 13 ማውረድ መቻሉን የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ ለምክር ቤት አባላት ከሰሞኑ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ሚኒስቴር ዴኤታው ይህን ይበሉ እንጂ እዳው መቼ? እንዴትና ለየትኛው እዳ ተከፈለ የሚለውን የማያመላክት እንደሆነና ከሁሉም በላይ ደግሞ የዓለም አቀፍ ተቋማት የሀገሪቷ እዳ ከፍ ማለቱን የሚያመላክቱ መረጃዎች እያወጡ ባሉበት ወቅት መሆኑ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ተጨማሪ ግልጽ የሆነ ማብራሪያ ሊሰጥበት እንደሚገባ ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስትያየታቸውን የሰጡ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶክተር ጉቱ ቴሶ የሀገሪቷ እዳ ባለፉት አምስት አመታት 25 በመቶ ከፍ ማለቱን የሚያመላክቱ አለማቀፋዊ መረጃዎች አሉ ብለዋል፡፡ አሁን ላይ የሀገር ውስጥና የውጭ የእዳ ጫና 68 ነጥብ 9 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር መድረሱን የሚያመላክቱ መረጃዎችም በተመሳሳይ እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ባለፉት በርካታ አመታት በአማካይ ሀገሪቷ የነበረባት እዳ የውጭ ንግዷን 150 በመቶ ይበልጥ አንደነበር አመላክተዋል፡፡
ሌላኛዉ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ አቶ ክቡር ገና መረጃው ግልፀኝነት የሚጎድለው የተሟላ መረጃ አለመሆኑን በማመላከት ተከፈለ የተባለው እዳ ግን ባለፉት አመታት ላይሆን ይችላል የሚል ግምት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ አይ ኤም ኤፍ በቅርቡ የሀገሪቷ የውጭ ንግድ ደካማ መሆኑን አመላክቷል ያሉ ሲሆን ፤ የሀገሪቷ እዳ ከአስር በመቶ ዝቅ ለማድረግ የታቀደው እቀድ መልካም ቢሆንም በምን መልኩ ነዉ የሚለው ሊታወቅና ማብራሪያ ሊሰጥበተ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
ገንዘብ ሚኒስቴር ባለፉት የሪፎርም አመታት 10 ቢሊዮን ብር የሀገሪቷ እዳ ተከፍሏል እንዲሁም መንግስት ከፍተኛ ወለድ ያላቸውን ብድሮች እየተበደረ አይደለም ብሎ ከገለጸዉ መረጃ ባለፈ በተብራራ መልኩ የትኞቹ ብድሮች ናቸዉ የተከፈሉት የሚለዉ ባለመገለጹ ተጨማሪ ማብራሪያ ያስፈልገዋል ሲሉ ባለሙያዎቹ ጠቁመዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ