ጥር 22 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) በከፍተኛ ትምህርትና የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፍ ውስጥ ጥራትን አስጠብቆ ለመቀጠል ተቋማትን ኦዲት ማድረግ እንደሚገባ መገለጹን ተከትሎ ለትግበራ ቅድመ ስልጠና እንደሚያስፈልግ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ተገልጿል።
ለተቋማቱ የጥራት መለኪያውን ረቂቅ አሰናድቶ ለማጸደቅ እየሰራ ያለው የኢፌድሪ ትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ሲሆን ትምህርት ሚኒስቴር ደግሞ ስልጠናዎችን ለተቋማቱ በመስጠት ቅድመ ሁኔታዎች እንዲሟሉ እንደሚያደርግ በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጦሽኔ ለመናኸሪያ ሬዲዮ ተናግረዋል።
በቅርቡ ሳምንታት ውስጥ መመሪያውን የማጸደቅ ስራ የሚሰራ ይሆናል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ቀጥሎ መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ሆነ ለቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፍ ስልጠና መስጠት አስፈላጊ ነው ሲሉ ተናግረዋል። በመሆኑም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይህንን ሃላፊነት እንደሚወጣም ሚኒስትር ዴኤታዉ ገልጸዋል። የጸጥታ ችግር ባሉባቸው አካባቢዎች የመመሪያውን ተተግባሪዊነት በተመለከተ ላነሳንላቸው ጥያቄ፣ የቱንም ያህል ያልተሟሉ ጉዳዮች ቢኖሩም መመሪያ በየትኛውም ስፍራ መተግበር እንዳለበት ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።
ከአዲሱ የጥራት ኦዲት መመሪያ ጋር በተያያዘ ምንም እንኳን መለኪያው በትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ቢወጣም በመለኪያው ተመርቶ በተቋማቱ ላይ የመጨረሻውን እርምጃ የሚወስደው የትምህርት ሚኒስቴር መሆኑን የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን የቴክኒክና ሙያ የጥራት ኦዲት ዴስክ ሃላፊ አቶ ጎበዜ ይመር ተናግረዋል። መመሪያው ጸድቆ ወደ ትግበራ ሲገባ የኦዲት ግኝቶቹን በቀጥታ ለትምህርት ሚኒስቴር የመላክ አሰራር ነው የሚኖረው ሲሉም አቶ ጎበዜ ገልጸዋል።
የከፍተኛ ትምህርትና የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፍን ጥራት ለማስጠበቅ በሚል በቅርቡ ሊጸድቅ እየተሰናዳ ያለው የኦዲት መለኪያ መመሪያ ከአተገባበሩ አንጻር በብዙዎች ዘንድ ጥያቄ ማስነሳቱን ቢቀጥልም አስፈላጊና የማይቀር መሆኑ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ተገልጿል።
ምላሽ ይስጡ