እ.ኤ.አ በ2015 በፈረንሣይ ፓሪስ ከተማ የዓለም ሀገራት ስምምነት ያደረጉበት አማካይ የሙቀት መጠን ጭማሪን ከሁለት ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በታች በበቂ ሁኔታ እንዲቀንስ እና በተቻለ መጠን በ1.5 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ መገደብን እንደ ህግ የሚያስቀምጥ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ዝቅተኛ የካርበን ልቀትን መተግበር እና የሙቀት መጠን መጨመርን ለመቆጣጠር የሚረዱ ሥራዎችን በመስራት በተለይም የደን ልማትን ማጠናከር ላይ ትኩረት የሚያደርግ በዚህ ስራ ታዳጊ ሀገራትን መደገፍንም ያካትታል፡፡
ተመራጩ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸው ከዚህ ስምምነት እንድትወጣ ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡ይህንኑ አስመልክቶ ሃሳባቸውን ለመናኸሪያ ሬዲዮ የሰጡ የአካባቢ ጥበቃ እና የህግ ባለሙያዎች ውሳኔው ለታዳጊ ሀገራት ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፍ ደረጃ በአየር ንብረት ለውጥ (የአለምን ሙቀት ለመቀነስ የሚደረገውን እንቅስቃሴ የሚያደናቅፍ ነው ብለዋል፡፡
በተለይም አሜሪካ ከፍተኛውን የካርበን ልቀት ከሚፈጥሩ ሀገራት መካከል እንደመሆኗ ከዚህ ስምምነት መውጣቷ ተገቢነት ባይኖረውም፤ ስምምነቱ አስገዳጅ ባለመሆኑ ተጠያቂ እንዳትሆን ያደርጋታል ሲሉ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያው ዶ/ር ይተብቱ ሞገስ ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል አለም አሁን ላይ የደረሰችበት የሙቀት መጠን ከዚህ በላይ ከጨመረ የተለያዩ ክስተቶች እንዲፈጠሩ እና ለመኖር አዳጋች እንደሚሆን፤ አዳጊ ሀገራትም ይህን ለመከላከል በሚያደርጉት ስራ ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥር መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ይህንኑ ሃሳብ የሚያጠናክሩት የህግ ባለሙያው አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ፤ ዶናልድ ትራንፕ እያሳለፏቸው ያሉ ውሳኔዎች በተለይም ለአዳጊ ሀገራት ትልቅ ተፅዕኖ የሚያሳድር ነው ብለዋል፡፡ ይህ ውሳኔያቸው ሌሎችንም ሀገራት የሚቀሰቅስ እና ስምምነቱን የሚያፈርስ ከመሆኑም ባለፈ አሜሪካ በተለያዩ ዘርፎች ለሚደረግ እንቅስቃሴ ደጋፊ ነኝ የሚለውን አቋሟን የሚጣረስ ተግባር ነው ብለዋል፡፡
ውሳኔው በአለም አቀፍ ደረጃ በህግ እና በመርህ እንዲሁም በስምምነቶች መሰረት የሚደረጉ ነባር አካሄዶችን የሚጥስ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚደርስባቸውን ተፅዕኖ ለመቋቋም እንዲያስችላቸው ያደጉና ፈቃደኛ የሆኑ አገሮች የገንዘብ፣ የቴክኖሎጂና የአቅም ግንባታ ድጋፍ እንዲያደርጉ ግዴታ የሚያስቀምጥ ቢሆንም አሜሪካ ከዚህ ስምምነት መውጣቷ አዳጊና ገና በማደግ ላይ ያሉ አገሮች በዚህ ስምምነት የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዳይወጡ የሚያደርግ፤ የአለም የሙቀት መጠን መጨመርን ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት የሚያደናቅፍ መሆኑን ባለሙያዎቹ ገልፀዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ