ጥር 13 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ከ27 ተቋማት ጋር በቅንጅት የተሰሩ ስራዎችን ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው ግምገማ፤ ባለፉት ስድስት ወራት ህገ ወጥ ንግድን እና አዋኪ ድርጊትን ጨምሮ ከ152 ሺህ በላይ የደንብ መተላለፎች ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ እንደገለፁት በመዲናዋ በተለያዩ ዘርፎች የሚስተዋሉ ህገ-ወጥ ተግባራትን ለመከላከል ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ገልፀው በተሰራው ስራ የደንብ መተላለፍ ጥሰትን ከባለፈው ተመሳሳይ ዓመት ጋር ሲነፃፀር 58 በመቶ መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል።
በዚህ መሰረትም በህገ ወጥ ንግድ፣ በአዋኪ ተግባራት፣በህገ ወጥ ማስታወቂያ እና በህገ ወጥ እንስሳት እርድ እና መሰል ተግባራት ላይ አስፈላጊው ቁጥጥር መደረጉን አንስተዋል።
ባለፋት ስድስት ወራት በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች ህገ ወጥ ንግድ በሚያከናውኑ 27 ሺህ 163 ህገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን አስረድተዋል።
በሌላ በኩል በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች ህገ ወጥ ግንባታ በሚያከናውኑ 27 ሺህ 163 ህገ ወጥ ግንባታ ላይ እርምጃ መወሰዱን አስረድተዋል።
በመዲናዋ በትምህርት ቤቶች ዙሪያ አዋኪ ተግባራት በሚፈጽሙ 3 ሽህ 486 አካላት ላይም እርምጃ መወሰዱንም ተገልፃል፡፡
ከዚህ ባለፈም ደረጃውን ያልጠበቀ ህገ ወጥ ማስታወቂያ በተለያዩ ቦታዎች በሚለጥፉ ከ88 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል ነው ያሉት፡፡
በአጠቃላይ ባለስልጣኑ በግማሽ ዓመቱ ህገ ወጥ ንግድን ጨምሮ በተለያዩ መሰል ጉዳዮች ላይ ደንብ በተላለፋ 152 ሺህ 521 አካላት ላይ እርምጃ መውሰዱን በሪፓርቱ ላይ ተመላክቷል፡፡
በተመሳሳይ የኮሪደርመሠረተ ልማት ደህንነት ለመጠበቅ ስራው በቀጥታ ከሚመለከታቸው 5 ተቋማት ጋር በመቀናጀት እና በተደራጀ መልኩ በኮሪደር ልማት ሊፈፀም የሚችልን የደንብ ጥሰት አስቀድሞ በመከላከል እና የደንብ ጥሰት ሲገኝም የእርምት እርምጃ በመውሰድ ከ135 ሚሊዮን ብር በላይ ለመንግስት ገቢ የማድረግ ስራ መሰራቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ መናገራቸውን ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ምላሽ ይስጡ