ጥር 09 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) ከጥር 10 እስከ ጥር 12 ቀን 2017 ዓ/ም ድረስ ጃን ሜዳ እና አቃቂ ቃሊቲ ታቦት ማደሪያ በሚከበረው የከተራና የጥምቀት በዓል ምክንያት የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር የተወሰኑ መንገዶች ለተሽከርካሪ ዝግ ስለሚሆኑ አሽከርካሪዎች አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
የ2017 ዓ/ም የከተራና የጥምቀት በዓል ያለ ምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር በጥምር የፀጥታ አካላቱ ቅድመ ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ስራ መገባቱ ይታወቃል። በዓሉ በሚከበርባቸው ቦታዎች ሁሉ ከአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ የስምሪት አቅጣጫን በመከተል ፀጥታ የማስከበር ተግባሩ የሚከናወን ሲሆን ከዚህም ጋር ተያይዞ ከጥር 10 ቀን 2017 ዓ/ም ጀምሮ በ11ዱም ክ/ከተሞች ጥምቀተ ባህር ባሉባቸው ቦታዎች ሁሉ በ500 ሜትር ክልል ውስጥ ታቦታት ሲወጡና ሲገቡ እንዲሁም በሚሄዱባቸው መንገዶች ለአጭር ጊዜም ይሁን ለረዥም ጊዜ ተሽከርካሪ አቁሞ መሄድ የተከለከለ መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል።
እንዲሁም ከጥር 10 እስከ ጥር 12 ቀን 2017 ዓ/ም ድረስ በጃን ሜዳ እና አቃቂ ቃሊቲ ታቦት ማደሪያ በሚከበረው የከተራና የጥምቀት በዓል ምክንያት በአካባቢው የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር፦
👉ከ6 ኪሎ አደባባይ – ምኒልክ ሆስፒታል
👉 ከምኒልክ ሆስፒታል – መከላከያ 3ኛ ሻለቃ አደባባይ
👉 ከ3ኛ ሻለቃ አደባባይ – 6 ኪሎ አደባባይ እንዲሁም አቃቂ ቃሊቲ አካባቢ
👉ከዋልያ ቢራ – ጥሩነሽ ቤይጂንግ ሆስፒታል
👉ከአቃቂ ዋናው መንገድ – ጥሩነሽ ቤይጂንግ ሆስፒታል
👉ከ08 – አቃቂ ድልድይ ድረስ ከጥር 10 ቀን 2017 ዓ/ም ከጠዋቱ 4:00 ሰዓት ጀምሮ መንገዱ ለተሽከርካሪዎች ዝግ ስለሚሆን አሽከርካሪዎች አማራጭ መንገዶችን መጠቀም እንደሚገባቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
ምላሽ ይስጡ