ጥር 09 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) መንግስት የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት ቀጣይነት ለማረጋገጥና የማህበረሰቡን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ የኢፌድሪ መንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
ሚንስትሩ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በመንግስት የተቀረጹ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራዎች የኢኮኖሚ እድገትን እዉን እንዲያደርግና የህብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ እንዲለዉጥ በሁሉም ዘርፎች እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ እየገነባች የምትገኘዉ ኢኮኖሚ ተለዋዋጩን የዓለም ሁኔታ ያገናዘበ፣ ነባር አቅሞችን በማጠናከር ወደ አዳዲስ ዘርፎች የሚያሻግር፣ የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ የሚያበረታታና የሚያጠናክር እንዲሁም የፈጠራ ስራዎችና የዲጂታል ኢኮኖሚዉን ወደ ፊት የሚያስፈነጥር ነዉ ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
በተጨማሪም እድገቱ የተቃና ኢኮኖሚን በመገንባት ለግብርናው፣ ለማኑፋክቸሪንግ፣ ለማዕድን፣ ለቱሪዝም፣ እንዲሁም ለዲጂታል ኢኮኖሚው ሚዛናዊ ትኩረት የሚሰጥ ሲሆን፣ ዘላቂ የልማት ፋናንስ ስርዓትን በመፍጠር ሀገራችንን ከብድር ጫና የሚያላቅቅ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
ማሻሻያዉ ለሀገር በቀል ኢኮኖሚዉ ምሰሶ የሆኑትን አራት መሰረታዊ ጉዳዮች ማለትም በሀገሪቱ የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚን መፍጠር፣ የንግድ ስራዎችን የሚያሳልጡና ዉጤታማነትን የሚያረጋግጡ፣ የንግድና ኢንቨስትመንት አካባቢን ማሻሻል፣ የዘርፎችን ምርታመነትና ዉጤታማነትን የሚያሻሽል እና የመንግስትን የማስፈጸም አቅም ማዕከል ያደረገ ነዉ፡፡
መንግስት በቀጣይ የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ እንዲኖር ለማስቻል በሁሉም ዘርፎች ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ እና በንግድ ስርዓቱ ዉስጥ ያሉ ችግሮችን በመፍታት በገቢያዉ ዉስጥ በቂ ምርት እንዲኖር ማድረግ የመንግስት ትኩረት መሆኑንም ዶ/ር ለገሰ ገልጸዋል፡፡ መንግስት ይሄንን በተሟላ ሁኔታ እየተገበረ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡
ከማክሮ ኢኮኖሚ ጭማሪ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ጉዳዮች በማህብረሰቡ ላይ ጫና እንዳያሳድሩ መንግስት ሀላፊነት በተሞላበት ሁኔታ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን ሲያከናዉን ቆይቷል ያሉት ሚኒስትሩ፣ መሰረታዊ ሸቀጦች ያለምንም ከልካይ ወደ ሁሉም ቦታዎች እንዲደርሱ መደረጉንም አስታዉሰዋል፡፡ በተመሳሳይም ህገ ወጦች ላይ ጠንካራ ቁጥጥር በማድረግ የእርምት እርምጃ ተወስዷልም ብለዋል፡፡
መንግስት ለመሰረታዊ ሸቀጦች መለትም ለአፈር ማዳበሪያ፣ ለዘይት፣ ለነዳጅ፣ ለመድሃኒት፣ ለገጠርና ለከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት እንዲሁም ለመንግስት ሰራተኞች ጨምሮ በዓመት ከ400 ቢሊዮን በላይ ድጎማ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ስለሆነም ጫናዎችን በመጋራት የኢኮኖሚ እድገት ቀጣይነትን ማረጋገጥ ከሁሉም ዜጎች የሚጠበቅ ሀገራዊ ሀላፊነት እንደሆነ ሚኒስትሩ ማስገንዘባቸውን አገልግሎቱ አስታውቋል፡፡
ምላሽ ይስጡ