እግዱ የተጣለባቸው ፓርቲዎች ግን ውሳኔው ተገቢነት እና ህጋዊ መሰረት የሌለው ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን እንደ አገር በቅርቡ ከሚጠብቋቸው ትልልቅ ብሔራዊ ጉዳዮች መካከል አገራዊ ምክክር፤ የሽግግር ፍትህ እና 7ተኛው አገራዊ ምርጫ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ አገራዊ የምክክር ኮምሽን እንደ ሀገር ያላግባቡ፤ ለጠብ እና ብጥብጥ አብሮም በአንድነት ለመቀጠል ማነቆዎቸ ናቸው ባላቸው ጉዳዮች ላይ መክሮ ከስምምነት ለመድረስ አገር እና ህዝብን ለማሻገር አጀንዳዎችን በማሰባሰብ እንዲወያዩበት ለማድረግ ለ3 ዓመት የጊዜ ቆይታ የተቋቋመ ድርጅት እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ኮምሽኑ እስካሁን የጸጥታ እና መረጋጋት ችግሮች ካለባቸው የአማራ እና ትግራይ ክልል ውጪ በሁሉም የአገሪቱ አከባቢዎች አጀንዳ የማሰባሰቡን ስራ እንዳጠናቀቀ ገልጿል፡፡
ቀጣይም ከፍተኛ የፖለቲካ ጡዘት አለባቸው በሚባሉቱ ክልሎች የሚሰበሰበው አጀንዳ እንደ ሀገር ግብዓት የሚሆኑ ሀሳቦች ይነሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ኮምሽኑ አስታውቋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ ከሚጠብቋቸው አበይት ጉዳዮች መካከል አንዱም ይኸው አገራዊ ምክክር ነው፡፡
ባለፈው ጊዜ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በነበረው ጦርነት በመደበኛው የህግ ስርዓት መዳኘት የማይችሉ ሰፋፊ የህግ ጥሰት እና ኢ-ሰብዓዊ ወንጀሎች መፈጸማቸውን ተከትሎ በይቅርታ፤ ምህረት እና ተጠያቂነትን በማስፈን ተበዳይን ለመካስ በሚል የሽግግር ፍትህ እንደሚያስፈልግ ከስምምነት ተደርሶ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ መውጽደቁም የሚታወቅ ነው፡፡
በጦርነቱ ወቅት ውስብስብ እና ሰፋፊ የህግ ጥሰት የፈጸሙትን ተጠያቂ ለማድረግ ተበዳዮችንም ለመካስ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ተግባራዊነት ሌላው እንደ አገር ከሚጠበቁት ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳል፡፡
ሌላው አበይት ተጠባቂ ሀገራዊ ጉዳይ በቀጣይ ዓመት የሚካሄደው 7ተኛው አገራዊ ምርጫ ነው፡፡ ምርጫ የዲሞክራሲ ስርዓትን የሚከተሉ አገራት ዜጎች በሰላማዊ መልኩ ግልጽ፤ ፍትዓዊ እና ተዓማኒነት ባለው መልኩ በድምጻቸው መሪያቸውን የሚመርጡበት ሒደት ነው፡፡
በአህጉራችን አፍሪካ ይህ የዴሞክራሲ ልምምድ ገና በእንጭጭ ደረጃ እንዳለ ነው ዛሬም ድረስ የሚገለጸው፡፡ ለአብነት ባለፈው እ.ኤ.አ በ2024 የምዕራብ አፍሪካ አገራት ማሊ፤ ኒጀር፤ ጊኒ እና ቡርኪናፋሶ መሪዎቻቸውን ከሰላማዊ የምርጫ ሒደት ይልቅ በመፈንቅለ መንግስት ገልብጠው በወታደራዊ አገዛዝ እየተዳደሩ እንዳሉ ይታወቃል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፖሊሲ አማካሪ፤ በአፍሪካ ህብረት የጸረ-ሙስና አማካሪ ቦርድ ሊቀመንበር፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር በመሆን ያገለገሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ፤ በአሁኑ ሰዓት በአፍሪካ ሂዩማኒተሪያን አክሽን ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ ናቸው፡፡
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ባደረጉት የዳሰሳ ጥናት በአፍሪካ ባለፉት 50 ዓመታት 200 የሚጠጋ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተደርጎ 110 የሚጠጋው የተሳካ የመንግስት ግልበጣ የተደረገበት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ይህም የሆነበት ምክንያት በአህጉሪቱ የዲሞክራሲ ልምምድ ገ ያልዳበረ፤ የዜጎች ጥያቄ በሰላማዊ መልኩ ስለማይፈታ፤ መሪዎችም አንዴ ስልጣን ከያዙ ቶሎ የማይለቁ በመሆናቸው ነው ይላሉ፡፡ በሰላማዊ መልኩ ተካሄደ የተባለውም ምርጫ ውጤቱ ተጭበርብሯል በሚል ህዝባዊ ተቋውሞ አመጽ እና ብጥብጥ እንደማያጣው በቅርቡ የተደረገው የጋቦን እና ሞዛምፒክ ምርጫ አመላካች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያም በቀጣይ ዓመት 7ተኛውን አገራዊ ምርጫ ታከናውናለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ቀጣዩ አገራዊ ምርጫ እየተጠበቀ ባለበት በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተለያዩ ጥሰቶችን ፈጽመዋል ያላቸውን 11 ፓርቲዎችን፡- የኦሮሞ ነጻነት ንቅናቄ፤ አንዲ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፤ የጌዲዮ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፤ የሐረሪ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት፤ የገዳ ስርዓት ለኦሮሞ ነጻነት ፓርቲ፤ የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ፤ አዲስ ትውልድ ፓርቲ፤ የጋምቤላ ብሔራዊ ንቅናቄ፤ የጋምቤላ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ፤ የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ህብረት እና አገው ለፍትህ እና ለዲሞክራሲ ፓርቲን/ በቀን 11/02/2017 ዓ/ም በጻፈው ደብዳቤ እንዳገዳቸው ይታወቃል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 5ቱ ፓርቲዎች /የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ፤ አዲስ ትውልድ ፓርቲ፤ የጋምቤላ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ፤ የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ህብረት እና አገው ለፍትህ እና ለዲሞክራሲ ፓርቲዎች/ ማሻሻያ አድርገዋል በሚል ቦርዱ እግዳቸውን አንስቷል፡፡
በ2018 ዓ/ም 7ተኛው አገራዊ ምርጫ እየተጠበቀ ባለበት በዚህ ወቅት የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ተጠናከረው ለምርጫው መፎካከር ሲገባቸው ከወዲሁ መታገዳቸው በቀጣዩ አገራዊ ምርጫው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚፈጥር አንዳንዶች ይገልጻሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ውሳኔው ፓርቲዎችን ከማጠናቀር አንጻር አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዳለው የሚገልጹም አልቀሩም፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ ከ1984 ዓ/ም ወዲህ በኢትዮጵያ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት መሰረቱን የያዘ ነው እና በህግም የፓርቲዎች መብት እየተረጋገጠ የሄደበት ጊዜ ነው ብለዋል፡፡
በዚህ ጊዜ እየተለመደ የመጣ ባህል አቅም ያላቸው ፓርቲዎችን ተንጠልጥሎ የመውጣት ነገር እንደተለመደ ገልጸዋል፡፡ ከመንግስት የሚገኘውን በጀት ለመጠቀም በሚል የሚቋቋሙ ፓርቲዎች እየተፈጠሩ እንዳሉ አመላክተዋል፡፡
ለአብነት በበጀት ዓመቱ 65 ሚሊየን ብር በቦርዱ በጀት አቅራቢነት መንግስት መድቦ ለፓርቲዎች የተከፋፈለው ብለዋል፡፡ይህንን ጥቅም ለመቀራመት በማሰብ ብቻ የሚደራጁ ፓርቲዎች እንዳሉም ነው የገለጹት፡፡
ቦርዱ ፓርቲዎች ጠንካራ ርዕዩት ዓለም ይዘው ለፖለቲካ ስልጣን የሚታገሉ የዲሞክራሲ አካሔዱን ወደ ፊት የሚያመጡ ፓርቲዎች እንዲኖሩ እንጅ ድጎመን መሰረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ እና የድጎማ ፖለቲከኞችን ወደ ፊት ማምጣት አይደለም ማለታቸው ይታወቃል፡፡ በመሆኑን ቦርዱ ፓርቲዎቹ ላይ እግድ የጣለው ጠንካራ፤ ተወዳዳሪ እና የዲሞክራሲ እና ፖለቲካ ምህዳሩን ሊያሰፉ የሚችሉ ፓርቲዎችን ይፈጥራል የሚል እምነት በመያዝ ነው ብለዋል ምክትል ሰብሳቢው፡፡
የእግድ ውሳኔው አላማ እና ግብ የሌላቸው ፓርቲዎች የፖለቲካ ምዕዳሩን እንዳያጣብቡ ያደርጋል የሚል እምነት እንዳለ ያመላከቱት ምክትል ሰብሳቢው፤ ይህም ካልተሳካ ሌላ አማራጭ ይዘረጋልም ነው ያሉት፡፡
እገዳው እስካሁን ከተጣለባቸው ፓርቲዎች አንዱ የሆነው የኦሮሞ ነጻነት ንቅናቄ ፓርቲ ነው፡፡ የፓርቲው ሊቀ-መንበር አቶ ደረጀ በቀለ አሁንም ቢሆን ቦርዱ ያስተላለፈውን ውሳኔ እንደማይቀበሉት እንዲሁም ቦርዱ በደብዳቤ ለእያንዳንዱ ፓርቲ ማሳወቅ ቢኖርበትም በግል ለፓርቲያቸው በደብዳቤ ያሳወቀው ነገር እንደሌለ እና ይህም ህጋዊ አካሔድ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ ተገቢ እና ህጋዊ አግባብ የሌለው ነው ብለዋል፡፡
የአንድ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ዋና ሰብሳቢ አቶ ሲሳይ ደጉ በበኩላቸው “የቦርዱ ውሳኔ አልገበንም፤ ቀደም ብለንም ከቦርዱ ጋር በክስ ሒደት ላይ ነው ያለነው” ብለዋል፡፡
11ዱ ፓርቲዎች ከመታገዳቸው በፊት የአንድ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ በ2016 ዓ/ም እንደታገደ ነው ያስረዱት፡፡ዋና ሰብሳቢው ፓርቲው የአሰራር ችግር ካለበት ተጣርቶ በህግ ውሳኔ ሲሰጠው ነው መታገድ ያለበት እንጅ በዚህ መልኩ አይደለም ባይ ናቸው፡፡ ቦርዱ ከዚህ ቀደም ከበጀት አጠቃቀም እና ጉድለት ጋር በተያያዘ በፓርቲው ላይ ክስ እመሰርታለሁ ብሎ በፓርቲው አመራሮች ላይ እግድ እንደጣለ ያስታወሱት አቶ ሲሳይ፤ ቦርዱ የእግድ እርምጃ ከመውሰዱ በፊት በህግ አግባብ ጠይቆን ማብራሪያ እና ምላሽ መስጠት ሲገባን ይህን እንድናደርግ እድል ሳይሰጣን ነው ያገደን፤ ህግ ጥሷል ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡

እንደ ሰብሳቢው ሀሳብ የአንድ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ጉዳይ በህግ እየታየ ሳለ ነው ሌላ ተጨማሪ ውሳኔ የተወሰነበት፡፡ የስነ አመራር እና የፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያው አቶ ጌትዬ ትርፌ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ ተገቢ እና ከዚህም በላይ ጠንካራ መሆን እንደሚገባው አመላክተዋል፡፡ አቶ ጌትዬ “ግለሰቦች ማህተም እና ሰርተፊኬት እየያዙ በፓርቲ ስም የሚነግዱ የቦርዱን በጀት ለማጭበርበር የሚሰለፉ፤ ህዝብ ሳይወክላቸው በህዝብ ስም የሚነግዱ እየተበራከቱ ስለሆነ የቦርዱ ጠንካራ እርምጃ አስፈላጊ ነው” ብለዋል፡፡ ቦርዱ በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ከማድረግ በተጨማሪ ምቹ እና ሰፊ የፖለቲካ ምሕዳር እንዲፈጠር መስራትም፤ ፓርቲዎችን ማጠናከር ላይም መስራት ይጠበቅበታል በዚህ ረገድ ክፍተት አለበት ብለዋል፡፡ ጠንካራ እና ተወዳዳሪ የሚያደርግ አቅም የሌላቸው ፓርቲዎች ወደ ፊት እንዳይመጡ ውሳኔው ገዳቢ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመላክተዋል፡፡ በመሆኑም በቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥር ሳይሆን ፓርቲዎችን ይበልጥ የሚያጠናክር ነው ባይ ናቸው፡፡
የህግ ባለሙያው አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገራዊ ምርጫ መሳተፍ ግዴታቸው መሆኑን ያብራራሉ፡፡ ከዚያ በፊት ግን የህጋዊነት መርህን ማሟላት እንዳለባቸው ነው የሚናገሩት፡፡ አቶ ጥጋቡ የህጋዊነት መርህ የሚባለው ፓርቲዎች ወቅቱን የጠበቀ ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ፤ ፖለቲካዊ ፕሮግራማቸውን ለአባላት እና ደጋፊዎቻቸው ማስተዋወቅ እንደሆነ እና ይህም በቀዳሚነት የሚጠበቅባቸው ኃላፊነት መሆኑን አብራርተዋል፡፡ አቶ ጥጋቡ “እንደ አጋጣሚ ሆኖ በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ስሪት ብሔር ተኮር ነው፤ ይህም ፓርቲዎች በአከባቢያዊ የብሔር አደረጃጀት እንዲታጠሩ አድርጓቸዋል” ብለዋል፡፡
በመሆኑም ይላሉ ባለሙያው “ሰፊ ራዕይ ያለው፤ አገርን ወደ ተሻለ ጉዞ የሚወስድ በርካታ አባላት እንዲኖራቸው የሚያስችል የፖለቲካ ፕሮግራም የላቸውም ለምሳሌ የኦሮሞ ህዝብ የስልጣን ባለቤት እና የልማት ተጠቃሚ መሆን አለበት ብለው የሚታገሉ ከ13 እስከ 15 የሚጠጉ አከባቢያዊ ፓርቲዎች አሉ ነገር ግን አንድም የውሃ ጉድጓድ አላስቆፈሩም አንድም ትምህርት ቤት አላስገነቡም፤ እንወክለዋለን ለሚሉት የኦሮሞ ህዝብ አንዳች ያመጡት ነገር የለም” ብለዋል፡፡
ደካማ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሻለ የልማት ፕሮግራም በሚዘረጋ ፓርቲ እንደሚወጡ የሚያብራሩት ባለሙያው፤ በተመሳሳይ በትግራይ ክልል ከ5 እስከ 6 የሚሆኑ ፓርቲዎች እዳሉና ነገር ግን ተወደዳዳሪ እና አሸነፊ የሚያደርጋቸው ባለቸው ሰፊ ራዕይ እና ተሻጋሪ የፖለቲካ ርዕዩት አለም እንጂ በቁጥራቸው መብዛት አይደለም ይላሉ፡፡
በመሆኑም ምርጫ ቦርድ ያገዳቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች የታገዱት በራሳቸው የአሰራር ክተት እንደሆነ ነው የሚያምኑት፡፡ ለአብነት አብዛኛው ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ እንደማይጠሩ፤ በቂ አባላት እንደማያፈሩ፤ ፖለቲካዊ ፕሮግራማቸውን እንደማያሳውቁ ገልጸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ከህጋዊነት መርህ እንዲወጡ እንዲታገዱ እንዲሰረዙ ያደርጋቸዋል ሲሉም አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም ቦርዱ የወሰነው ውሳኔ ህጋዊነትን የተከተለ ነው ባይ ናቸው፡፡
የህግ ባለሙያው “እነዚህ ፓርቲዎች ሳምሶናዊት ፓርቲ ይባላሉ ቲተር እና ማህተም ይዘው በየስብሰባ አዳራሹ የሚንቀሳቀሱ፤ አባላት አምጡ ሲባሉ የሚያቀርቡት አባል የሌላቸው ናቸው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
እንደ የህግ ባለሙያው ማብራሪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ6ቱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ የጣለው የእግድ ውሳኔ ህጋዊነት ያለው ተገቢ እንዲሁም በኢትዮጵያ ጠንካራ እና ተፎካካሪ መሆን ያልቻሉ ፓርቲዎችን የሚያከስም፤ ሰብሰበብ ያሉ በቁጥር ያነሱ ግን ደግሞ ጠንካራ ፓርቲዎችን ለማፈፍራት የሚያስችል፤ ተጠናከሮም መቀጠል ያለበት ነው፡፡ በቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ጠንካራ እና ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ለማፍራት የቦርዱ ጠበቅ ያለ እርምጃና ፓርቲዎችን የማብቃት፤ የፖለቲካ ምዕዳሩን የማስፋቱ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው ባለሙያዎቹ ያመላከቱት፡፡
በቀጣይ ዓመት በሚደረገው 7ተኛው ሐገራዊ ምርጫ የምርጫ ቴክኖሎጂዎች ተግባራዊ እንደሚደረጉ ያስታወቀው ቦርዱ፤ ከዚህ ቀደም የነበረው አዋጅ 1162/2011 ክፍተቶች የታዩበት በመሆኑ በአዲስ መልኩ ረቂቅ አዋጅ ማዘጋጀቱንም ገልጻል፡፡ ከማሻሻያው አንዱ የምርጫ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ እንዲደረግ የሚል ሲሆን በተጨማሪም የፖለቲካ ፓርቲዎች በአስገዳጀነት ሴቶችን ተሳታፊ እንዲያደርጉ፤ ነፃ የመሰብሰቢያ አዳራሽ እንዲያገኙ፤ ፓርቲዎቹ ጥፋት ከተገኘባቸው ከዚህ ቀደም እንዲወገዱ የሚለውን ውሳኔ በመቀየር ለ5 አመት ታግደው እንዲቆዩ የሚል ውሳኔ እንደተካተተበት ተገልጻል፡፡ እንዲሁም ከምርጫ በኋላ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በምክክር እንዲፈታው የሚል ሀሳብም እንደተካተተበት ተመላክቷል፡፡

ምላሽ ይስጡ