ወጣቶች በሃገር ላይ ከፍተኛዉን አስተዋጾዖ የማድረግ ሃይል እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ ታድያ የወጣቶች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተለያዩ ፖሊሲዎች ቻርተሮች እና አለምአቀፍ ስምምነቶች ሲወጡና ሲፈረሙም ይስተዋላል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ወጣቶች ቻርተርን በአዋጅ ቁጥር 817/2006 ማጽደቋን መረጃዎች ያመላክታሉ። ሆኖም ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ አገራት ለወጣቱ ሰፊ ሕዝባዊ አንቀሳቃሽ ፖሊሲና ምቹ ሁኔታ በመንደፍ ረገድ፣ ብዙ ጉድለት እንዳለባቸው የሚናገሩ ብዙ ናቸው፡፡
አለማቀፋዊ ስምምነቶች ወጣቶች መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶችን ምንም አይነት ልዩነት ሳይደረግባቸው ሙሉ በሙሉ መጠቀማቸውን የሚገልጽ ነው፡፡
በኢትዮጵያ እየተፈጠሩ ያሉ አለመግባባቶችን በምክክር ለመፍታት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር የወጣቱን ጥያቄ ቅሬታ እና የወጣቱ ሃሳብ ይንጸባረቅበታል ተብሎ ከሚጠበቀዉ ሃገራዊ ሁነት መካከል ሃገራዊ ምክክሩ አንዱ ነዉ።
የሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ወጣቶችን ከማሳተፍ እና በሃገር ውስጥ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ከማስጠበቅ አኳያስ ምን እየሰራ ነው በሚለው ጉዳይ የሃገራዊ ምክክር ኮሚሽንን ጨምሮ በኮሚሽኑ ውይይት ወቅት የተሳተፉ ወጣቶችንና የዘርፉ ባለሙያዎችን ተዘዋውረን አነጋግረናል፡፡
ለኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን የወጣቶችን አጃንዳ ይዘው በምክክሩ የተሳተፉ ወጣቶች እንደሚሉት ከሆነ ላለፉት ወራት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት አስፈላጊ ያላቸውን አጃንዳዎች ቢቀበልም ኮሚሽኑ የወጣቶችን አጀንዳ ለመረከብ የሄደበት ረቀት እዚህ ግባ የማይባል መሆኑን አንስተዋል፡፡
በምክክር ኮሚሽኑ ውስጥ ሲሳተፉ ያገኘናቸው ዩቡንቱ ወጣቶች ለሰላም ጥምረት የተባለ ግብረሰናይ ድርጅት አንዱ ነው፡፡ ይህ ድርጅት ወጣቶችን ወክሎ ኮሚሽኑ ምክክር ሲያደርግባቸው በነበሩት ቦታዎች ሁሉ በመዘዋወር የወጣቶችን ሃሳብ ሲሰበስብ መቆየቱን ገልጾ ኮሚሽኑ በተለያዩ ሰባት ከተሞች እና ወረዳዎች ድረስ በመሄድ የተለያዩ አጀንዳዎችን መሰብሳበ እንደተቻለ የተናገሩት ወጣቶቹ፤ እንደሃገር ለወጣቶች እየተሰጠ ያለው ትኩረት ዝቅተኛ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
የኢትዮጵያ ቀጣይነትን ለማስጠበቅ የወጣቶች ሃላፊነት መሆኑን የሚናገሩት የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው አቶ ወንድሙ ደግፍ፤አሁን የሚታየው የወጣቶች ችግርና ሸክም ከዓምናውም ሆነ ከሌላው ጊዜ የባሰ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ጥራት ያለው ትምህርት ካለማግኘት በተጨማሪ ራስን ለማሻሻልና ለመለወጥ ያሉ ዕድሎች መጥበባቸው ዋናው ችግር መሆኑን አንስተው ይህም በምክክሩ ዘርፍ ላይ ተካታች መሆን እንደሚገባው ጠቁመዋል፡፡
የወጣቱን የኑሮ ሸክም የሚያቀሉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን ከማበጀት በተጨማሪ፣ ከግጭትና ከሰላም ዕጦት ችግር የወጣቱን ሕይወት የመታደግ ከባድ ሸክም አሁን ላይ ሃገር የሚመራው መንግሥት እንደተጫነበት አንስተው በዚህ ውስጥ የምክክር ኮሚሽኑ የወጣቶችን አጀንዳ በተገቢው መንገድ ካልተረከበ ፋይዳ እንደማይኖረው የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው ተናግረዋል፡፡
በብዙ የፖለቲካ መድረኮች ወጣቶች በአደረጃጀት ወይም በውክልና ሲሳተፉ እንደሚታይ የሚናገሩት የስነ አመራር መምህርና ፖለቲከኛው አቶ ጌትየ ትርፌ፤ በቅርቡ የምክክር ኮሚሽኑ ስትራቴጂክ ዕቅዱን ሲያስገመግም ወጣቶች ራሳችንን ችለንና የራሳችንን አጀንዳ ይዘን የምንቀርብበት መድረክ ቢመቻች የሚል ጥያቄ ማቅረባቸው ጎልቶ ተነስቶ እንደነበር ይናገራሉ፡፡
ከዚህ ይልቅ እንደ ቀደሙ አስተዳደሮች ሁሉ በተለያዩ አደረጃጀቶች የወጣቱን ድምፅ የማስተጋባት ዝንባሌ እንደሚታይ አንስተው ይህ ደግሞ መንግሥት የወጣቱን ነባራዊ ችግሮች ለማድመጥና ለመፍታት ዕድል አይሰጠውም የሚል ሥጋት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽኑ ወጣቶችን በምን መልኩ ማሳተፍ እንዳለበትና እንዴት እያሳተፍ እንዳለ ሊለይ እንደሚገባ ፖለቲከኛው አንስተው ትክክለኛውን ወጣት በማሳተፍ ሃገርን በመገንባትና በመቆም ለአለመም የሚተርፍ ኢትዮጵያዊ ወጣትን ማፍራት እንደሚቻል ይናገራሉ፡፡
ከአጀንዳ አቅራቢዎች ጀምሮ በነበረው የምርጫ ሂደት ላይ በትክክል ኢትዮጵያዊ ወጣቶችን የሚወክሉ አጀንዳ አቅራቢዎች መመረጣቸው እንደሚያጠራጥራቸው የስነ አመራር መምህርና ፖለቲከኛው አቶ ጌትየ ትርፌ ገልጸዋል፡፡
ወጣቶች ሃገር ተረካቢ እንደመሆናቸው በወጣቶች የሚቀርቡ አጀንዳዎች የሃገሪቱን እጣፋንታ የሚወስኑ እንደሆኑ የሚናገሩት የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዋና ዳይሬክተር አቶ ተረፈ ዳጊቶ ናቸው፡፡
ወጣቶችን ያሳተፈ ወጤታማ የምክክር ሂደትን መጠቀም ከተቻለ የሃገርን ዘላቂ ሰላም ማስጠበቅ እንደሚቻል አንስተው በተቃራኒው ከሆነ ግን የልማት እጦት ፤ የግጭት ምክንያት እንደሚሆን ነው ዋና ዳይሬክተሩ የሚናገሩት፡፡
የወጣቶችን አጀንዳ ገደብ ሳይሰጥ የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሊቀበል እና እንደሃገር በወጣቶች ላይ የሚነሱ ክፍተቶችን ለማረቅ ሊሰራ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዋና ዳይሬክተር አቶ ተረፈ ዳጊቶ ተናግረዋል፡፡
ከ4 መቶ በላይ የሚሆኑ የወጣቶችን አጀንዳ ተቀብለው እንደነበር የሚናገረው ደግሞ ዩቡንቱ ወጣቶች ለሰላም ጥምረት ግብረሰናይ ድርጅት የወጣቶች ተወካየች ወጣት መሃመድ ኢብራሂም ለወጣቱ አስቸኳይ መፍትሄን ይሻሉ የተባሉ አስር አጀንዳዎችን መርጠው ለሃገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ማስረከባቸውን ያስታውሳል፡፡
በተለይም ሃገሪቱን ወደተሻለ እድገት ሊያመጡ ይችላሉ ተብለው የተመረጡ ሦስት ዘርፎችን ለኮሚሽኑ እንዳስረከቡ ወጣቱ ይናገራል፡፡
ኮሚሽኑ ከወጣቶች የቀረበለት አጀንዳ እንደ አንድ የመወያያ አጀንዳ ሊያደርገው እንደሚገባ የሚናገረው ወጣት መሃመድ ከወጣቶች ምክንያታዊ መሆን ይጠበቃል ይላል፡፡
የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለማገዝ የወጣቶችን አጀንዳ ሲሰበስብ የነበረው ዩቡንቱ ወጣቶች ለሰላም ጥምረት ግብረሰናይ ድርጅት ነው፡፡
ድርጅቱ እስካሁን ኮሚሽኑ በደህንነት ስጋት ምክንያት የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ ባልጀመረበት የትግራይ እና የአማራ ክልል ድረስ በመሄድ በክልሎቹ የሚገኙ የወጣቶችን አጀንዳ እንደተቀበለ የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ብሩክ ይርጋለም ተናግረዋል፡፡
በተለይም ኮሚሽኑ ስራ ባልጀመረባቸው አካባቢዎች ላይ አጀንዳዎችን ለመቀበል ተቸግረው እንደነበር ይናገራሉ፡፡
ኮሚሽኑ ሁሉንም ማህበረሰብ አካታች ለማድረግ እየሞከረ እንደሆነ የሚያነሱት ሊቀመንበሩ ሰላማዊ ኢትዮጵያን ለመፍጠር በቅድሚያ ወጣቶች ላይ መስራት አስፈላጊ እንደሆነ በዓፅንዖት ተናግረዋል፡፡
ለዘላቂ ሰላምና ለተረጋጋ ሀገረ መንግስት ግንባታ የወጣቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን የሚገልፁት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ በሃገራችን የሚታዩ የሃሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶች የሚንፀባረቁት በወጣቶች መሆኑን ይናገራሉ፡፡
በዚህም በቅድሚያ ተጎጂ የሚሆኑት ወጣቶች በመሆናቸው ኮሚሽኑ በሄደበት እርቀት ልክ የወጣቶችን አጀንዳም እየተቀበለ እንዳለ ተናግረዋል፡፡
በሃገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የተሰበሰቡ እና በተለያዩ አደረጃጀቶች ወደ ኮሚሽኑ የመጡ የወጣት አጀንዳዎች ኮሚሽኑ የሃገሪቱን ወጣት ይወክላሉ ብሎ እንደሚያምን ቃል አቀባዩ ይናገራሉ፡፡
በአፍሪካ ብሎም በኢትዮጵያ ለወጣቶች የሚሰጡ ትኩረቶች ዝቅተኛ መሆናቸውን ሃሳባቸውን ያሳፈሩ ተሳታፊዎች እና ታዛቢዎች ገልጸዋል፡፡በኢትዮጵያ ሃገራዊ ሰላም አስጠብቆ ለመቀጠልና ሃገር ተረካቢ ዜጋን ማፍራት እንዲቻል በሃገሪቱ እየተከናወነ በሚገኘው የሃገራዊ ምክክር በቀዳሚነት ወጣቶችን አሳታፊ ማድረግ እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡
የስራ አጥ ወጣቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩ የተገለጸ ሲሆን ይህም ለማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች አለመረጋጋት ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ ተመላክቷል፡፡ የወጣቶችን የትምህርት ደረጃን ከማሳደግም ባሻገር ተሰጥቷቸውን ሊያሻሽሉ የሚችሉበትን ምቹ ምህዳር በመፍጠር ኢትዮጵያ ከወጣቶቿ መጠቀም ይገባታል ተመላክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ወጣቶች ከሃገራቸው አልፈው ለሌሎች አለማት የሚጠቅሙ እንዲሆኑ ለማስቻል ችግር ፈቺ ትምህርትን ከመስጠት አኳያ ሁሉም ተቋማት ሊሰሩ እንደሚገባም ተገልጿል፡፡
ምላሽ ይስጡ