Conflict Management and African Politics በሚለው መጽሃፉ ላይ ቴረንስ ላዮንስ ሲጠቅስ ፡ የአመለካከት ልዩነት፣ መቃረን፣ አለመግባባት ወይም መረጋጋትና አንድነትን የሚያጠፋና ያጠፋ እንደሆነ ነው ግጭት የሚባለው ይላል። ደራሲው ካሁን ቀደም The Puzzle of Ethiopian Politics በሚለው መጽሃፉም ይታወቃል። እናም ደራሲው ሲቀጥል ግጭት ማለት ደግሞ ይላል አዎንታዊ ትርጓሜ ያላቸው እንደ ሰላም፣ አንድነት፣ መስማማት፣ መግባባት፣ ፍቅር፣ እርቅ፣ ድርድርና መከባበር የመሳሰሉት ጉዳዮች አለመኖር ወይም መጥፋት ማለት ነው ይላል። የመንግስታቱ ድርጅትም እንዲሁ ሰላም ማለት የጸጥታ መደፍረስ አለመኖር ብቻም ሳይሆን ከዚያም ከፍ ያለ እሴት ስለመሆኑ ይናገራል። ለዚሁ ግንዛቤው ይመስላል እንደውም፣ በየአመቱ መስከረም 21 ቀን የአለም የሰላም ቀን እንዲከበር ድርጅቱ ደንግጓል። ልክ የአለም ባንክና አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ዘመናዊው የምጣኔሃብታዊ እድገት አተያይ መስተካከል አለበት ብለው እድገት የሚለካው በጥቅል ኢኮኖሚያዊ ምንዳጌ ሳይሆን ሰዎች በሚኖሩት ህይወት ላይ ባለው ለውጥ ነው እንደሚሉት ሁሉ ተመድም የሰላም ህልውና መለካት ያለበት ከግለሰቦች የስሜትና የአእምሮ መረጋጋት ጀምሮ መሆን እንደሚኖርበት በየአመቱ በሪፖርቶቹ ያስገነዝባል። አለም ከሰላም ይልቅ ለግጭትና ለጦርነት ረብጣ ቢሊዮኖችንና ትሪሊዮኖችን ታወጣለች ሲል ተመድ (የተባበሩት መንግስታት ድርጅት) ይገልጻል። እናም እንደ ተመድ ግምት በየአመቱ በትንሹ እስከ አንድ ትሪሊዮን ዶላር ለግጭት ይፈሳል ይላል።
ግጭትና ጦርነቶች ሲከሰቱ ውይይትና ድርድር በየትኛውም ነባራዊ ሁኔታዎች ውስጥ ያለና የሚመከር መሆኑን ምሁራን ይናገራሉ። ድርድር የሚያስፈልገውም በዋናነት በሁለት ምክንያቶች ነው ይባላል፡፡ በአንድ በኩል ከድርድሩ ውጪ ያሉ አማራጮች ከፍ ያለ ዋጋ የሚያስከፍሉ ከሆነ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ያለድርድር ምንም አይነት መፍትሄ የማይገኝ ሲሆን ነው ይላሉ የአለም አቀፍ የህግ ባለሙያው አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ።
ክልላዊና ሀገራዊ ፈታኝ ሂደት፦
ባለፉት ቅርብ አመታት ኮቪድና የሰሜኑ ጦርነት እንደ ሀገር ፈታኝ ሆነው መቆየታቸው ይታወቃል። አሁን ላይ ደግሞ በተለይም በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ግጭትና ጦርነት መጠነ ሰፊ ጉዳት እያስከተለ የቀጠለ መሆኑ ይታወቃል። ይህንን በፋኖ እና በመንግስት መከላከያ ሰራዊት መካከል ያለ ግጭት ለማብረድና አቀራራቢ ድልድይ እንዲሆን በሚል በክልሉ የሰላም ካውንስል ሰኔ 2016 ዓ.ም ተቋቋሟል። ምንም እንኳን ካውንስሉ ስራውን ከጀመረ አጭር ጊዜ ቢሆንም ከተቋቋመ ጊዜ አንስቶ በተለይም በሁለቱ ተዋጊ ሃይሎች መካከል ያለውን ግጭት ለማብረድ አቅም እንደተሳነው ይነገራል። ካውንስሉ የሚለው እኔ አደራዳሪ አይደለሁም የማደራደር ስልጣኑም አቅሙም የለኝም ነው። ነገር ግን ማቀራረብና ሰላማዊ መፍትሄ እንዲኖር የማድረግ ሚና መሃል ሆኖ ለመጫወት ነው የተቋቋምኩት ይላል። በመሆኑም ካውንስሉ እስካሁን በሄደባቸው የሙከራ ሂደቶች በሁለቱም ሃይሎች ዘንድ መተማመን ያለ አይመስልም ሲሉ የሰላም ካውንስሉ የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ እያቸው ተሻለ ይናገራሉ።
በተደጋጋሚ ጊዜ በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኩል እንደሚታየውም ሪፖርት በአማራ ክልል በተከሰተው ግጭት ምክንያት በርካታ ተማሪዎች ትምህርት እየተማሩ አይገኙም፣ የጤና መሰረተ ልማቶች ከፍተኛ ችግር ገጥሟቸው ወረርሺኝና ሌሎችም በሽታዎችን በቶሎ ለማከምና መድሃኒቶችን ተደራሽ ለማድረግ የክልሉ የጸጥታ ችግር ከፍተኛ እንቅፋት ፈጥሮባቸው እንደሚገኝ ሲገልጽ ቆይቷል። በክልሉ እልባት ባጣው የሁለቱ ሃይሎች ጦርነት የተነሳ በርካታ ሴቶች ተደፍረዋል፣ ህጻናትና አቅመ ደካሞች ለስደትና ለሞት ተዳርገዋል፣ ርሃብ ተከስቶ ብዙዎችን ለሞትና ለአደጋ እንዳጋለጠም የኢሰመኮ የሁልጊዜ ሪፖርት ሆኖ ዘልቋል። እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶችም በቀላሉ ለተጎጂዎችና በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ሰዎች እርዳታ ማቅረብ አልቻሉም። ይህንን አቶ እያቸውም ያምናሉ ፣ በክልሉ በርካታ ሰብአዊም ቁሳዊም ኪሳራ ደርሷል በማለት አሁንም አቅማቸው እንደፈቀደ መሃል ገብተው የማቀራረብ ስራን ለመስራት ጥረት እንደሚያደርጉ በመግለጽ ለጊዜው ግን ምንም አይነት አዎንታዊ ሂደትና ለውጥ እንዳላስገኙ ገልጸዋል።
በክልሉ ውስጥ ጦርነቱ ይዞታውንና መልኩን እያሰፋ በመላ አማራ ክልል በስፋት እየተካሄደ በመሆኑ አካል ጉዳተኞች፣ ተፈናቃዮች፤ ሴቶችንና ወጣቶችን የጎዳና እየጎዳም ያለ ሂደት ሆኗል ሲሉ አቶ እያቸው ተናግረዋል። ካውንስሉ የሀገር ውስጥ ተቋሟትንና አለም አቀፍ የውጭ ተቋማትንም አካቶ ግጭቱን ለማብረድ አሁንም በመስራት ላይ እንደሚገኝ የሚናገሩት የካውንስሉ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ካውንስሉ ጥረት ከማድረግ የዘለለ ፋይዳም የለውም ምንም ያሳካው ጉዳይ ባይኖርም አሁንም ግን በጥረታቸው እንደሚቀጥሉ ነው ህዝብ ግንኙነት የተናገሩት።
ካውንስሉን ሁለቱም ተዋጊ አካላት ሊሰሙት ፈቃደኞች አልነበሩም አይደሉምም ያ ባለመሆኑ ተገቢ ያልሆኑ ጉዳቶች እንደቀጠሉ ናቸው ያሉት አቶ እያቸው እንዲህ ያሉ ግጭቶች በተፈጥሯቸው ጊዜና አጋጣሚዎችን መጠቀምና መጠበቅ የሚፈልጉ በመሆናቸው ምንም እንኳን ቀውሱ የሰውን ህይወት እየቀጠፈ ቢገኝም ጊዜ እየጠበቅን በማደራደር ማመናችንን እንቀጥላለን ብለዋል።
ካውንስሉ የአጭር ጊዜ የምስረታ ህይወት ያለው ብቻ መሆኑ ሳይሆን ገና በሎጂስቲክና በገንዘብ አቅም በቅጡ ያልተደራጀ መሆኑ አብሯቸው አስተባብሮ እሰራለሁ ካላቸው አካላት ጋር በመስራት አላማውን ለማሳካት አልቻለም ሲሉም ህዝብ ግንኙነት ሃላፊው ያስረዳሉ። ይህ አንዱ ፈተና ነው የሚሉት አቶ እያቸው ሌላኛውና ዋነኛው ለካውንስሉ ፈተና የሆነው የሁለቱ ተዋጊ ሃይሎች ከፍተኛ አለመተማመን ነው ብለዋል። የሁለቱ ሃይሎች አለመተማመን ካውንስሉንም ጭምር ወደ አለማመን ተሻግሯል በማለት ካውንስሉን አንዴ ከፋኖ ወገን ሲላቸው ደግሞ ከመንግስት ወገን በሚል ስም የማጥፋት ስራም እየተሰራባቸው ስለመሆኑ አቶ እያቸው ተናግረዋል።
በክልሉ መንግስት በኩል ለካውንስሉ ጥያቄዎችና የሰላም ሂደቶች በቂ ትኩረትና ምላሽ አለመስጠትም እየቀጠለ የሚገኝ ተግዳሮት ነው፡ ይህ ሁሉ ፈተናዎች ተጋርጠውብን ነው አሁንም የአቀራራቢነት ሚናችንን ለመወጣት ተስፋ ባለመቁረት የምንሞክረው ሲሉ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊው ተናግረዋል።
በክልሉ በተፈጠረው ዘርፈ ብዙ ቀውስ ምክንያት የሃይማኖት አባቶች ከፍተኛ ሃላፊነትን ይዘው በክልሉ ከሚገኙ የሀገር ሽማግሌዎችም ሆኑ ከሌሎችም ጋር መስራት እንደሚጠበቅባቸው ሲነገር መቆየቱ አይዘነጋም። ከዚህ አንጻር ለመናኸሪያ ሬዲዮ ሃሳባቸውን የሰጡ የክርስትናም የእስልምናም ዘርፍ የሃይማኖት አባቶች፣ ክልሉ ከሰላም ውጭ ምንም አማራጭ የለውም ቤተ እምነቶችም የየእለት አስተምሯቸው ይሄው ነው ሲሉ ተናግረዋል። በላሊበላ ከተማ በቤተ ኡራኤል የሚያገለግሉት አባት ሲናገሩ፣ እንደ ሀገር በጦርነትም ሆነ በሰላም ወቅት የሃይማኖት አባቶች ሚና ላቅ ያለ ነበር ሲሉ መልአከ ሰላም አባ ይስሃቅ ተናግረዋል። ታጣቂዎቹን በአካል ባናናግርም በየእለቱ በአውደ ምህረት ማህበረሰቡን በማስተማርና ለታጣቂዎቹም ስለ ሰላም ሲሉ እንዲማጸኑ በያለንበት የፈጣሪ ቃል ተገን አድርገን ጥረት በማድረግ ላይ እንገኛለን ብለዋል። እንዲሁም በባህር ዳር ከተማ የእስልማ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሰራተኛ ሼህ አህመድ ኡመር የሃይማኖት አባቶች የሚናገሩትና የወጣቱና የማህበረሰቡ እንቅስቃሴ ለየቅል መሆን እንደማይገባው ያስረዳሉ። አባቶቹ እንዳሉት የክልሉ የግጭት ሁኔታና ስፋት ቅዳዜና አዛንም እስከማቋረጥ የደረሰበት ወቅት እንደነበረ በማስታወስ አሁን ላይ ከክልሉ የሰላም ካውንስል ጋር በመቀራረብ ሰላም እንዲሰፍን ጥረት ለማድረግ እየሞከርን ነው ብለዋል።
በክልሉ ላለው የሰላም ምኞት ማህበረሰቡ ብቻ ሳይሆን ተዋጊ ሃይሎቹም ይሁነኝ ብለው የአባቶችን ግሳጼና ምክር ሊያደምጡና ሊታዘዙ ይገባ ነበር ይህ ባለመሆኑ ቀውሱ ቀጥሏል ሲሉ የድርጊቱን አሳዛኝነት ገልጸዋል።
ለወትሮው በሰላምና መረጋጋት የሚታወቀው ክልል አሁን ለወጣቶች የስጋት ምንጭ፣ ተስፋ የጨለመበት ክልል ሆኗል ይህ አሁን ላለነው ወጣቶች እንደ መከራ የሚቆጠር ነው ሲሉ ሃሳባቸውን ያጋሩን ደግሞ በፎኖተ ሰላም ከተማ የወጣቶች አደረጃጀት አባል ናቸው። ሁሉም ታጣቂ ሃይሎች በገዛ ሀገራቸው ላይ የጦርነት አውድማ እያበጁ ያሉት የሚሉት ወጣት በሪሁን ንጋቱ አሁን ወጣቱ ሰርቶና ተንቀሳቅሶ ክልሉንም እራሱንም ማሳደግ ሲገባው ፣ ሰርቶ መኖርም ፣ ተምሮ መጨረስም ሆነ አድጎ ቤተሰብ መመስረትም ቀቢጸ ተስፋ የሆነበት ክልል ሆኗል ይላሉ። ወጣት በሪሁን ሰርተው ሮጠው አምርተው በመብያቸው ትምህርትም ስራም ያቆሙት በዚሁ በክልሉ ባለው ግጭት ምክንያት መሆኑን ያስረዳሉ። በሰላም ካውንስሉ በኩል የሚሰማው ሁለቱም ተዋጊ ሃይሎች አይተማመኑም የሚል ነው፣ እኛም እንግዲህ እንደወጣት በሁለቱም በኩል የጠራ ግንኙነት ተፈጥሮ ችግሩ በቶሎ ቢቋጭና ታጣቂዎችም አሁን ባለው ሁኔታ ከውድመት በቀር እየሄዱበት ያለው አካሄድ ጠቃሚ አለመሆኑን አውቀው መንግስትም ልዩነቶችን ቀርቦ አድምጦና ሰዶ ከማሳደድ ተቆጥቦ ለጋራ ለሆነ ሀገርና ክልል ሁለቱም ሃላፊነት ቢሰማቸው መልካም መሆኑን ወጣት በሪሁን ተናግረዋል። የጦርነቱ ስፋት ነገ ከነገ ወዲያ በሰላማዊ ቀዬ በየቤታቸው ያሉትንም የሚበላ ነው ያሉት ወጣት በሪሁን መሽቶ ሲነጋ ተስፋ ለመሰነቅም አዳጋች እንደሆነባቸው ገልጸዋል።
እንደ ሀገርም እንደ ክልልም አብዝተን የመናናቅና የመገፋፋት ባህል ክፉኛ እያዳበርን ነው ፣ ይህ የትም አላደረሰን ወደየትም አልወሰደን ይልቁንስ አሁን ወደገባንበት አዘቅት ውስጥ ነው የጨመረን ሲሉ በባህር ዳር የሚኖሩት ሌላኛው የከተማው የወጣቶች አደረጃጀት ዘርፍ አባል ወጣት ይልቃል ታምሩ ነግረውናል። ክልሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚሰሩ ወጣቶችን በሚፈልግበት በዚህ ዘመንና ወቅት ባልተገባ ጦርነት ውስጥ ወድቆ ወጣቶች ተስፋ የሚሰንቁበት ሳይሆን የሰቆቃና የስቃይ ክልል ተፈጥሮላቸው ብዙዎችን ረግተው እንዳይማሩ፣ ተዟዙረውና ተንቀሳቅሰውም እንዳይሰሩ እንዳደረጋቸው ወጣት ዘመድኩን ጎሹ ይናገራል። ወጣቱ አሁን ላይ በቂ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በክልሉ ባለመኖሩ ምክንያት እሱም ቤተሰቡም በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ተናግሯል።
በሺዎች የሚቆጠር ተፈናቃዮች በመጠለያ ካንፕ ውስጥ የምንገኘው ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ እስካሁንም በክልሉ በዘለቀው ጦርነት ምክንያት ነው ሲሉ የነገሩን ደግሞ በደብረ ብርሃን ቻይና መጠለያ ካምፕ ውስጥ ያሉ ወ/ሮ አልማዝ እያዩ የተሰኙ ጎልማሳ እናት ናቸው። በተለይ በክልሉ ደብረብርሃንን ጨምሮ በወሎ አካባቢም ያሉ ተፈናቃይ ህጻናት፣ እኛቶች፣ አባቶችና አቅመ ደካሞች በርካታ በመሆናቸው ክልሉ ላይ ሰላም ማምጣት ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ አልነበረም ይላሉ።
ከክልሉ ሰላም እጦት ጋር በተገናኘ መናኸሪያ ያነጋገራቸውና ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ በጎጃም ደብረወርቅ ከተማ ሕክምና ሙያ ላይ የተሰማሩ አንድ ባለሙያ በየጊዜው በሚነሳው ግጭት ምክንያት መንገድ በመዘጋጋቱ እሳቸው በሚያገለግሉበት የሕክምና ተቋም ታማሚዎች ተጨማሪ ሕክምና ሲጠይቁ ለሪፈራል መላክ አለባቸው ተብሎ ከታመነ፣ ባጃጆች አቆራርጠው አንዱ ለሌላው እያሸጋገሩ አቋራጭ መንገዶችን በመፈለግ በጫካ ለመሄድ ይገደዳሉ ይላሉ። ይህ ብቻም አይደለም አስቀድሞም በመንገድ መዘጋት ምክንያት የተለያዩ ፋታ የማይሰጡ ወረርሽኞችም ሲከሰቱ ሃኪም መድረስ ሳይቻላቸው ባሉበት ህይወታቸው የሚያልፈው ብዙ ነው ብለዋል።
በክልሉ ያለው ግጭት የፈጠረውን እክል የክልሉ ርእሰ መስተዳድርም ሆነ የፌደራል መንግስት አልሸሸጉም። ይልቁንስ ካሁን ቀደም በሰጡት መግለጫ ሁለቱም አካላት ሃሳብ አስተላልፈው ነበር።
ከ8.5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ተገዝቶ ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት ሲሞከር ታጣቂ ሃይሉ እንቅፋት ሲፈጥር እንደነበር፣ እንዲሁም በኢንቨስትመንት ዙሪያ ወደ አካባቢው ኢንቨስተሮች እንዳይመጡ ታጣቂ ቡድኑ አካባቢ ሰላም አይደለም በሚል እያስነገረና መንገድም እየዘጋ በርካታ ተግዳሮት ፈጥሮ መቆየቱን የክልሉ መንግስት ርእሰ መስተዳድር ከቅርብ ወራት በፊት በስራ ሂደት ግምገማቸው ወቅት በሰጡት ማብራሪያ መግለጻቸው ይታወሳል።
በጥቅሉ በክልሉ በግጭቱ ምክንያት በቱሪዝም በዘርፉ፣ በንግድ እንቅስቃሴውና በትምህርት ላይም እንቅፋት መፈጠሩን ያልካዱት ርእሰ መስተዳድሩ የክልሉ መንግስት በሰላም እጅ የሚሰጡትን በሰላም በመቀበል እጅ የማይሰጡትን ደግሞ ህግ የማስከበር ዘመቻውን እንደሚያስቀጥል ተናግረዋል።
ከሳምንታት በፊት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በሰጠው መግለጫ በበኩሉ በአማራ ክልል በታጣቂው ቡድን ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ የተነሳ በተለይም የትምህርት ስርአቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ መጎዳቱን አስታውቋል። በመሆኑም መላው የክልሉ ህዝብ በእኩይ ተግባር ላይ የተሰማሩትን ሃይሎች ከመንግስት ህግ የማስከበር ዘመቻ ጎን በመሰለፍ ሊገታ እንደሚገባውም የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ገልጸዋል። ሚኒስትሩ አክለውም በሰላም ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ የሚመጡ ታጣቂ ሃይሎችን መንግስት በሰላማዊ መንገድ እየተቀበለ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ታዲያ መፍትሄው ምን ይሁን?
የክልሉ መንግስት ካሁን ቀደም ሞክሮት የነበረውን ከታጣቂ ሃይሎች ጋር የመወያየት ጉዳይ በአዎንታዊነት ተመልክቶ ማስቀጠል እንደሚገባው የአማራ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ተስፋሁን አለምነህ ተናግረዋል። በክልሉ የሚገኙ ፖለቲካ ፓርቲዎችም ለሰላም ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸውና ምርጫ ጠብቆ አለሁ ከማለት እንዲህ ባለ ነውጥና ግጭት ወቅት ለማህበረሰቡ ሰላም ቀርቦ መስራት አስፈላጊ ስለመሆኑም ሰብሳቢው ይናገራሉ። አክለውም በዚህ ረገድ ተግባራዊነቱ ላይ ምን ያህል ርቀት ሂደናል የሚለው እንዳለ ሆኖ እንደ ምክር ቤት የጋራ አቋምና ስምምነት እንደነበረና አሁንም ምክር ቤቱ በቻለው ርቀት ልክ ለክልሉ ሰላም መስራት ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆን እንዳለበት አቶ ተስፋሁን ተናግረዋል።
በመንግስትና በፓርቲዎች በኩል ለሰላም ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ተገቢነቱ እንዳለ ሆኖ ታጣቂ ሃይሎችም በክልሉ እያደረሱ ካለው ዘርፈ ብዙ ኪሳራ አንጻር ሃላፊነት አለባቸው ሲሉ ደግሞ የሚናገሩት የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ጌትዬ ትርፌ ናቸው። ታጣቂዎቹ ይህን ያህል ጊዜ ሲቆዩ አላማቸው ምንድን ነው? እስከመቼስ ነው በእንዲህ ያለ ሁኔታ የሚቀጥሉት ? ከመንግስት ጋር በሚኖራቸውስ ድርድር ግልጽ የሆነ መዋቅርና ቡድናቸውን ወክሎ ለድርድር የሚቆም አካል አላቸው ወይ የሚለውን ቡድኑ በራሱ ሊመልሰው የሚገባ ጉዳይ ነው ሲሉም ተንታኙ ተናግረዋል። ነገር ግን እንደሚታየውና እንደሚሰማው ከሆነ ቡድኑ በተደራጀ መዋቅር ውስጥ የሚመራና ግልጽ የሆነ ራእይ ያለውም አይመስልም ሲሉ ባለሙያው ይናገራሉ።
ይህንኑ የፖለቲከኛውን ሃሳብ የሚጋሩት የሰላም ካውንስሉ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ እያቸው ተሻለ ሲያክሉ፣ ታጣቂ ቡድኑ ምንም አይነት ወጥ አደረጃጀት የለውም ይላሉ። በመሆኑም ካውንስሉ ሊሄድባቸው በሞከረው የማቀራረብ ሙከራዎች ውስጥ ይህ ነው የሚባል የጠራ ተወካይና አደረጃጀት የላቸውም ብለዋል። በሁለቱ ተዋጊ ሃይሎች በኩል ያለውን ክፍተት ችላ ብሎ አሁን የክልሉ መንግስትና ሌሎችም ሀገራዊና አለም አቀፋዊ ተቋማት ሰላማዊ ጣልቃገብነታቸው ላይ ጊዜ ሳይሰጡ ሊሰሩ ይገባልም ሲሉ አቶ እያቸው ገልጸዋል።
የቱንም ያህል በሁለቱ ተዋጊ ሃይሎች መካከል ክፍተት ቢኖርም ከሚፈርሱት መሰረተ ልማቶችና ከሚከሰተው ሰብአዊ ቀውስ አይበልጥምና በክልሉ የሚገኙ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ምሁራንና እራሳቸው ተዋጊ ሃይሎቹ ሰከን ብለው መነጋገር መቻል አሁን ላይ አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑን ተንታኙ አስረድተዋል።
ነሐሴ 2015 ዓ.ም በአማራ ክልል በመከላከያ ሠራዊትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተጀመረው ጦርነት እነሆ እንደ ቀልድ አንድ አመት ከአራት ወሩን እየተሻገረ ይገኛል። የጤና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች በግባቡ ማከምና ማስተማር እንዳይችሉ ግጭቱ እንከን ፈጥሮ ቆይቷል። 15 አባላት ያሉት አመቻች የሰላም ካውንስል ቢቋቋምም በካውንስሉ በራሱ ችግርና በክልሉ መንግስትም ድጋፍ አናሳነት ታክሎበት ይባስ ብሎ ለማደራደር ሲሞክር ተደራዳሪ የግጭቱ አካላት የእርስበእርስ መተማመን መጥፋት በክልሉ ለሚፈለገው ሰላም እንከን ፈጥሮ መቆየቱ ተገልጿል። ዛሬም በክልሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ትምህርት ቤት መሄድ ሳይችሉ የቀሩት በዚሁ ግጭት የተንሳ ነው።
በቀጠለው ጦርነት ወደ ክልሉ የሚገቡና የሚወጡ የሕዝብ አገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎች በተደጋጋሚ ስራ ሲያቆሙ ይታወሳል። በክልሉ በርካታ ሥራ ሲቆምና ዜጎች ለእንግልት፣ ለከፋ አደጋና ለተጨማሪ ወጪ ሲዳረጉም ተስተውሏል። ከአዲስ አበባ ወደ ጎጃምና ጎንደር መስመር የሚጓዙና ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ፣ በተመሳሳይ ወደ ደቡብና ሰሜን ወሎ፣ እንዲሁም ወደ ትግራይ የሚያመሩና የሚመለሱ አገር አቋራጭ የሕዝብ ተሽከርካሪዎች በአማራ ክልል ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ሥራ ላይ ናቸው ብሎ ያን ያህል ደፍሮ ለመናገር የሚያበቃ እንዳልሆነ ዞረን ያነጋገርናቸው የአገር አቋራጭ ሹፌሮችም አስረድተውናል።
በጦርነት እየታመሰ ባለው የአማራ ክልል መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ልኮ በተመረጡ የክልሉ የዞን ከተሞች መፍትሔ ያሻቸዋል ባላቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ሲያደርግ ቢቆይም፣ በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች መካከል የጀመረው ጦርነት ሊቆም አልቻለም፡፡
በክልሉ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ተገተው የቆዩበት፣የመንግሥት ተቋማት ሥራ የተስተጓጎለበትና የተዘረፉበት፣ የክልሉ ወጣቶች ከፍተኛ የሕይወት ዋጋ እየከፈሉ የነበሩበትና አሁንም የሚገኙበትም ለመሆኑ መናኸሪያ ያነጋገራቸው አካላት ምላሽ ማስረጃ ነው። በመሆኑም በክልሉ ያለውን ሰላም ለማምጣት የሚመለከታቸው መንግስታዊም ሆኑ የግል እንዲሁም አለም አቀፍ ተቋማት ሊረባረቡ እንደሚገባና እየቀጠለ የሚገኘውን ሰብአዊና ቁሳዊ ቀውሱን ሊታደጉ እንደሚገባ ነው የተመላከተው።
ምላሽ ይስጡ