የፖለቲካ ምህዳርን ማስፋትና ነጻ የሆነ ፖለቲካዊ ከባቢን መፍጠር ለዲሞክራሲና ለልማት ግንባታ አይነተኛ ቁልፍ ሚናን ይጫወታል በሚል ዛሬ ላይ የሰለጠኑ የምንላቸው ሀገራት በመርሁ ሲጠቀሙበት ይስተዋላሉ። ነጻና ፍትሃዊ በሆነ የፖለቲካ ስርአታቸው ምክንያት በሰለጠኑት ሀገራት ተፎካካሪ ፓርቲዎች በምርጫ ካርድ እሸነፋለሁ የሚል ወይም ምርጫ ተጭበርብሮ እወድቃለሁ የሚል ስጋት የለባቸውም ይልቁንስ ገና በተፎካካሪነት ወይም በተቃዋሚነት ጊዜያቸው ጀምረው የመንግስትን ፖሊሲ በመቃወምና በመሞገት ከገዢው መንግስት እኩል በየሀገራቸው ስርአት ላይ አዎንታዊ ሚና ሲጫወቱና ከፍ ያለ ተጽእኖም ሲያሳድሩ እንመለከታለን በሚል ይነገራል።
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የአፍሪካ አዳጊ ሀገራት ዘንድ ግን ፓርቲዎች እርስ በርስ በአላማ ሲራኮቱና የጸና አቋምና ራእይ አልባ ሆነው ከመፈጠራቸው ሲኮሰምኑ ወይም ሲኮላሹ ይስተዋላል ይላል እንግሊዛዊው በደቡብ አፍሪካ የአፍሪካ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በመተንተን የሚታወቀው ፓትሪክ ስሚዝ Why are Africa’s ruling former liberation parties in retreat? በሚል ሰሞንኛ ትኩስ ትንታኔው። የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች አስቀድመው ስልጣን ሳይዙ ነው ገዢውን መንግስት ሲያማርሩ የሚስተዋሉት የሚለን ስሚዝ ፣ ይህ በጥቅሉ የአፍሪካ ፖለቲካዊ ስርአት አውድ የፈጠረው ነው ይላል። ይሁን እንጂ ተስፋ ሰንቆ ገዢውን መንግስት በዲሞክራሲያዊ መንገድ በድምጽ እረታለሁ ከማለት ይልቅ ፍርሃታኣቸውን እያስቀደሙ መጠላለፍን እንደ ሁነኛ ቴክኒክ ይጠቀማሉ ይላል።
ኮሚሽኑ ቀጣይ አመት ከሚደረገው ብሄራዊ ምርጫ አንጻር ከፓርቲዎችና ከመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ የሚሰበሰበው አጀንዳ ሂደት እንዴት ይታያል?
በአፍሪካ የዲሞክራሲና ሰላም እንቅስቃሴ ታሪክ ሲታይ ድህረ ቅኝ ግዛት ጀምሮ የሚቆጠር የቅርብ ጊዜ ታሪክ ሆኖ እናገኘዋለን ይላሉ የታሪክ ምሁራን ስለጉዳዩ ሲናገሩ። በተለይ በአፍሪካ ከቅኝ ግዛት ማግስት የተሞከሩ የዲሞክራሲ ሂደቶች ቢኖሩም የምእራባውያኑ የረዘመ የተጽእኖ እጅ ስልቱን በቀየረ የኒዮ ኮሎኒያሊዝም መንገድ አህጉሪቷን በነጻ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ መንገድ እንዳትሄድ አሉታዊ በትር አሳርፎባታል ይላል ታዋቂው የታሪክና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ጋናዊው ዶ/ር ቪንሰንት ዶዶ ሲናገር። ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን የተሳናት አፍሪካ በበርካታ የአህጉሪቱ ሀገራት ከእርስበርስ የዜጎች ግጭት በተጨማሪ ሀገራዊ አንድነትንና መረጋጋትን አልፎተርፎም ሉአላዊነትን የሚፈታተን ሂደት ዛሬም ድረስ እየተከሰተ እንደሚገኝ ይታወቃል። ከነዚህ ሀገራት ተርታ የተሰለፈችው ኢትዮጵያ በተለይ ከቅርብ አመታት ወዲህ በየቦታው በሚነሳ የጸጥታ ችግር ምክንያት እክል ሲገጥማት ትስተዋላለች። የተለያየ ጥያቄን አንግበው በየጥጋቸው የቆሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገራዊ አንድነት ሲባል ተቀራርበው በጠረጼዛ ዙሪያ እንዲነጋገሩና እንዲመክሩ እንደ ሀገር ሙከራ እየተደረገ እንደሚገኝ ይታወቃል።
ሀገራዊ አንድነትን ለማምጣትም ሁሉንም አካላት አካታች የሆነ ውይይትና ምክክር እንዲደረግ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን መቋቋሙም ይታወቃል። ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት 2014 ዓ.ም ጊዜ አንስቶ በርካታ አካላትን በሂደቱ ውስጥ በማናገርና አጀንዳቸውን በመሰብሰብ እንቅስቃሴ ውስጥ ቢገኝም ፡ ያው እንደሁልጊዜው ሁሉ አጀንዳ ማሰባሰብ ባላካሄደባቸው የሰሜኑ ክፍል የሚነሱት ጉድለቶች እንዳሉ ሆነው ዛሬም ሁነኛ አጀንዳን ከፖለቲካ ፓርቲዎች በበቂ ሁኔታ አናግሮ ከመሰብሰብ አንጻር በተለይም በቀጣይ አመት 2018 ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫ ከመጠበቁ አንጻር ከወዲሁ የፓርቲዎች አጀንዳ በቅጡ ቀርቦና ተሰብስቦ ውይይትም እልባትም አግኝቶ ቢሆን ኖሮ ሁኔታዎችን ለቀጣይ አበጃጅቶ ለመቅረብ ይበጅ ነበር ሲሉ ፖለቲከኛው አቶ ጌትነት ወርቁ ይናገራሉ።
ከዚህ በተጨማሪም ምክክር ኮሚሽኑ እንደ ምርጫ ቦርድ ካሉት ተቋማት አጀንዳ ከመሰብሰብ አንጻር ምን እየሰራ ነው የሚለው ሲጠየቅ ይስተዋላል። ይህም ብዙውን ጊዜ ከቀጣዩ አመት የምርጫ ጊዜ ከመቅረብ አንጻር የሚታይ ነው። የመገናኛ ብዙሃን ዘርፉም መረጃን ከማዳረስና ከመዘገብ በዘለለ እንደ ዘርፍ የራሳቸው አጀንዳ እንዳላቸው ሲናገሩ በመቆየታቸውና ኮሚሽኑም የዘርፉን አጀንዳ እሰበስባለሁ በሚል ሲናገር በመቆየቱ ከምን ደረሰ የሚለውን መናኸሪያ ለማጣራት ጥረት አድርጓል። ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ከመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ አጀንዳ እሰበስባለሁ ባለው መሰረት በየማህበራቱ በኩል በተወካዮቻቸው በኩል አጀንዳዎቻቸውን እያስገቡ ነው የሚገኙት ሲሉ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚዲያ ኮሙዩኒኬሽንና አጋርነት ዘርፍ አስተባባሪና የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ ነግረውናል።
እስካሁን ባለው ተሳትፏቸው የመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ በንቃት አጀንዳዎቻቸውን እያቀረቡ እንደሚገኙ የገለጹት ቃል አቀባዩ ምን ምን አጀንዳዎች ናቸው በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ሊቀርቡ የሚችሉት ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ የተነሱ አጀንዳዎችን ቀድመን የመናገር ጉዳይን አሰራራችን አይፈቅድም አይፈቅድም ሲሉ መልሰዋል።
መገናኛ ብዙሃን የምክክር ኮሚሽኑን ሂደት በነቂስ እግር በእግር በመዘገብና ለህብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ፣ ነገር ግን በሁለንተናዊ የስራ ሂደታቸውና ሊሰሩትና ሊሰማሩበት ከሚፈልጉት ፍላጎት አንጻር እነሱም እንደሌላው ተቋም ሁሉ የራሳቸው አጀንዳዎች አሏቸው እንደ ዘርፍ ሲሉ ሂደቶቹ በፍትሃዊነት እየተስተናገዱ መሆናቸውን አቶ ጥበቡ ተናግረዋል።
የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ይህንን ይበሉ እንጂ መገናኛ ብዙሃኖችና የዘርፉ ባለሙያዎች አስተያየት ግን ችግሮችን በመንቀስ ላይ ያጠነጠነ ነው። ሀገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ አዲስ ልምምድ ቢሆንም ማህበረሰቡ ለጉዳዩ ያለው ግንዛቤ ከሚጠበቀው በታች ሆኖ እንዳገኘው የሚናገረው ጋዜጠኛ እሱባለው ጋሻው፤ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በዚህ ረገድ የሰራው ሥራ በቂ የሚባል አለመሆኑን ይገልፃል። ይህም በሚሰባሰቡ አጀንዳዎች ጥራት ላይ የራሱን ጉድለቶች ይፈጥራል የሚል ምልከታ እንዳለውም ጋዜጠኛው ተናግሯል።
የህብረተሰቡን ግንዛቤ ከፍ ከማድረግ ጀምሮ በርካታ ሚናዎች ያሉት የመገናኛ ብዙኃን ዘርፉም ቢሆን የራሱን አጀንዳዎች ከማቅረብ እንዲሁም በእውቀት ላይ የተመሰረተ ዘገባን ለህዝብ ከማቅረብ አንፃር ክፍተቶች እንደሚታዩበትም ጠቁሟል። በተለይም በመንግስት ስር የሚተዳደሩ መገናኛ ብዙኃን የሀሳብ ብዝሃነትን ለማስተናገድ ያላቸው ፍላጎት አናሳ መሆኑ፤ መገናኛ ብዙኃን ሊወጡት የሚገባውን ሚና አናሳ እንዳደረገውም ሀሳቡን አጋርቷል። ይህም ኮሚሽኑ የሚነሱበት የገለልተኝነትና ሌሎች ቅሬታዎች በሚገባቸው ልክ አጀንዳ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል የሚለው ጋዜጠኛው፤ እነዚህ መገናኛ ብዙኃን የኮሚሽኑን ተግባራት በመንግስት መነጽር ብቻ የሚመለከቱና የሚዛናዊነት ችግር የሚስተዋልባቸው መሆናቸውን እንዳስተዋለ ተናግሯል።
መገናኛ ብዙኃንና ባለሙያዎቻቸው የራሳቸውን አጀንዳዎች ከማቅረብ አንፃር ያከናወኑት ግልጽ እንቅስቃሴ ስለመኖሩ መረጃ እንደሌለው የሚገልጸው እሱባለው፤ የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚያቀርበው አጀንዳ መኖሩ ግን ተስፋ ሰጪ መሆኑን አስምሮበታል። የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር በራሱ የውስጥ ችግሮች መተብተቡ የጋዜጠኞች ድምፅ በሚገባው ልክ እንዳይሰማ ማድረጉንም አከሎ አንስቷል። የመገናኛ ብዙኃን የባለቤትነት ጉዳይ፣ የመንግስት ጣልቃ ገብነትና ሀሳብን በነፃነት የመግልፅ መብት ጉዳይ አሁንም መፍትሄ የሚያሻቸው ጉዳዮች ቢሆኑም ሀገራዊ ምክክሩ ለነዚህ ጉዳዮች ትኩረት ይሰጣል የሚል ግምት የሌለው መሆኑን የሚናገረው እሱባለው፤ እንደ ሀገር ያሉት ችግሮች ሥር የሰደዱ መሆናቸውና የሀገርን አንድነት ከማስቀጠል ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባ መሆኑ የመገናኛ ብዙኃንን ጉዳይ ቅንጦት እንዳስመሰለው ምልከታውን አጋርቶናል። የመገናኛ ብዙኃንን ጉዳይ ከሀገራዊ ምክክሩ ባለፈ በመንግስት ላይ በሚደረጉ የተለያዩ ውትወታዎች መፍትሄ እንዲያገኝ መጣር ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባም ጠቁሟል።
መገናኛ ብዙሃን እንደ ዘርፍ የነጻነትና ሙያዊ ደህነንትን አስጠብቆ ከመስራት አንጻር አጀንዳ አላቸው ሲሉ ሃሳብ የሚያነሱት ደግሞ በአዲስ ማለዳ ሚዲያ ዋና አዘጋጅ ሆነው የሚሰሩት አቶ አማኑኤል ጀንበሩ ናቸው። ኮሚሽኑ በሚገኝበት አጀንዳ የማሰባሰብና የማወያየት ሂደት ውስጥ የገለልተኝነት ጥያቄ እንደሌሎቹ ሁሉ በኮሚሽኑ ላይ ከሚያነሱት አከላት መካከል አንዱ የመገናኛ ብዙሃኑ ዘርፍ ነው ሲሉም አቶ አማኑኤል ይናገራሉ። አክለውም የማህበረሰቡን ጥያቄዎች በተገቢው ጊዜና ስፍራ ሰብስበው ለእውነተኛ ሀገራዊ ሰላምና አንድነት ውጤት እየሰሩ ናቸው ወይ የሚለውንም እንደ መገናኛ ብዙሃን ዘርፍ እንጠይቃለን ይላሉ። በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ለሚቀርቡት ብቻ ሳይሆን በጥቅሉም በፓርቲዎችም ሆነ በሌሎች አካላት ዘንድ ብዙውን ጊዜ ወደ ሕገ-መንግስቱ የሚያመሩ ጥያቄዎችም በአጀንዳነት ሲነሱ ታዝበናል የሚሉት ዋና አዘጋጁ እነዚህን ጥያቄዎች ከቀጣይ አመት ምርጫ በፊት ኮሚሽኑ እልባት ሰጥቶ መሄድ ይችላል ወይ የሚለውም ላይ ስጋት አለ ሲሉ ይገልጻሉ።
ሌላው በዚህ ሂደት ውስጥ አስጊ ነው የሚባለው የመገናኛ ብዙሃንን አጀንዳዎች ሰብስቦ ለኮሚሽኑ ያቀርባል የተባለው ምክርቤት በራሱ ምን ያህል ገለልተኛና ታማኝ ነው የሚለው ነው በሚል አቶ አማኑኤል ይቀጥላሉ፡ ካሁን ቀደም የዘርፉን ችግር ተረድቶ ለባለሙያዎችም ለተቋማትም ጥያቄዎች የሚሰጠው ምላሽን በተመለከተ ያለው ልምድ እንብዛም የሚወደስ ሳይሆን ዳተኛ ነበር ሲሉም ከዚያ በመነሳት ከየመገናኛ ብዙሃኑ የተሰበሰቡትን አጀንዳዎች በፍትሃዊነት ተመልክቶ ከማድረስ አንጻርም ስጋት እንዳላቸው አቶ አማኑኤል ተናግረዋል። በተጨማሪም መገናኛ ብዙሃን ከፖለቲካ ተወዳዳሪዎቹ እኩል በቀጣይ አመት ለሚኖረው የምርጫ እንቅስቃሴ ሁነኛ ሚና ይኖራቸዋል ሲሉም ከወዲሁ በኮሚሽኑ ላይ የሚነሱት ጥያቄዎች ተፈትተው ሂደቱ በአዎንታዊነት መቀጠል ይገባዋልም ብለዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ታምራት ሃይሉ ፣ አጀንዳዎቻቸውን እንዲያስገቡ ለመገናኛ ብዙሃን ጥሪ መደረጉን ጠቅሰዋል። በጥሪው መሰረት አጀንዳዎች እየተሰበሰቡ እንደሚገኙና እስካሁን 79 ያህል አጀንዳዎች እንደተሰበሰቡ የገለጹት አቶ ታምራት ከእነዚህ አጀንዳዎች ውስጥ 19 የሚሆኑት የተመረጡ ሲሆን፤ በቀጣይ ወደ 5 እና 6 በማሳጠር አጀንዳውን የማስረከብ ሥራ እንደሚሰራ ነግረውናል።
ብሄራዊ ምርጫን በብዙ ዝግጅት እንደሚጠብቅ እንደ አንድ ሀገርና ምክክር ኮሚሽኑ ከተቋቋመለት አጀንዳዎችን ሰብስቦ ብሄራዊ መግባባትን የመፍጠር አላማ አንጻር በተለይም በጥያቄዎች መለያየት ምክንያት የግጭቶች አካልም ጭምር ሲሆኑ የሚስተዋሉት ፓርቲዎች አጀንዳ ጉዳይ ወሳኝና አንገብጋቢ ነው ይባላል።
ፓርቲዎች እንደ ፓርቲ በጋራ ምክርቤታቸው ውስጥ ለመምከር ሲሞክሩ ቢስተዋልም ብዙውን ጊዜ በራሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክርቤት ባለመግባባት ከሚጠቀሱ ምክርቤቶች ውስጥ ግንባር ቀደሙ ነው ይባላል ይላሉ ፖለቲከኛው አቶ ሃይሉ ከበደ።
በእኛ ሀገር ፖለቲካዊ አካሄድ የፖለቲካ ምህዳሩን መጥበብ እንደ ምክንያት በመጥቀስ ፡ የህዝብ አመለካከትና የፓርቲዎችም የውስጥ ድክመት ተጨምሮበት በተለይም በምርጫ ሰሞን ዜጎች ማንን እንመርጣለን በሚል ተስፋ እንዲቆርጡ እንዳደረገ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ህዝብ ግንኙነት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኢዩኤል ሰለሞን ይናገራሉ። የጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲ አለመብዛትም በፉክክር ፓርቲዎች ነጥረው በብቃት እንዳይወጡና መንግስትን እንዳይገዳደሩ ከማድረጉም በላይ ዜጎችም የሚበጃቸውን ለመምረጥ እድል እንዳያገኙ አድርጓል ይላሉ።
ዜጎች በዋናነት በተፎካካሪ ፖርቲዎች ተስፋ የሚቆርጡት በአንድ በኩል በራሳቸው አመለካከት ሲሆን አንድም ደግሞ በፓርቲዎች የስራ እንቅስቃሴ ድክመት አማካኝነት ነው ሲሉ የሚናገሩት ሌላኛው የፖለቲካ ፓርቲ የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ የአደረጃጀትና የአቅም ግንባታ ክፍል ሃላፊ አቶ ሙባረክ ረሺድ ናቸው። በተለይ ፓርቲዎች ምርጫ ሲመጣ ጠብቆ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የማድረግ ልማድ አለባቸው በማለት ይህ ከዝህቡ እንዲርቁና ርእዮተ አለማቸውም እንዳይታወቅ ያደርጋል ይላሉ።
እንደ ሀገር እስካሁን ድረስ ከትላንቱ የተሻለ አውድ ቢኖርም ዛሬም የምህዳር ጥበት በፖለቲካው ውስጥ ይታያል የሚሉት ፖለቲከኛው አቶ ሃይሉ ከበደ ደግሞ ፓርቲዎችም እንኳን ዘንቦብሽ አይነት እንኳን ጫና ኖሮባቸውና ምህዳሩ ጠባብ ነው ተብሎ እንዲሁም የመዋቅርና የጸና አላማ ችግር አለባቸው ይላሉ። አክለውም በጣት ከሚቆጠሩት በስተቀር ውስጣዊ ሀገራዊ አጀንዳቸውም የተጣረሰና ርቆ አሳቢ ሆነው ሲቀርቡ አይስተዋልም ይላሉ።
ለዚህ ምስቅልቅልና ለየቅል የሆነ አቋም ነው ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ያስፈለገውና ብሄራዊ መግባባትን ለመፍጠር በቅጡ አጀንዳቸውን ማወቅ የተፈለገው ሲሉ ሌላኛው የፖለቲካ ምሁርና ፖለቲከኛ አቶ ጌትነት ወርቁ ይናገራሉ።
ይህን ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚደረግ የአጀንዳ ማሰባሰብና ውይይት አካሄድ አስመልክቶ ታዲያ የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ ሲናገሩ በክልልና በከተማ አስተዳደሮች በኩል በተካሄዱ አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደቶች በሙሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፈው አጀንዳቸውን አንስተዋል ብለዋል። እንደ አቶ ጥበቡ ገለጻ ኮሚሽኑ ተቋማትንና ፓርቲዎችን ብቻ ሳይሆን ልዩ ልዩ አካላትን በማናገርና በማካተት ዘርፈ ብዙ አጀንዳዎችን እየሰበሰበ ነው በማለት ለሀገራዊ አለመግባባት ምንጭ ናቸው የሚባሉ ዶክመንቶችንም በመመርመር በምክክር ሂደቱ ውስጥ ያካትታል ብለዋል። በቅርቡም ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር ፓርቲዎች ውይይት በማድረግ ላለመግባባታቸው ምክንያት ነው ያሉትን ጉዳይ አንስተዋል ፣ ይህ አይነቱ አካሄድም ለምክክር ኮሚሽኑ ጥሩ የሚባል ግብኣት ስለሚፈጥር ከምርጫ ቦርድ ጋር እንደ ተቋም የሚወያዩት ጉዳይ ፍሬያማ እንደሚሆን አቶ ጥበቡ ተናግረዋል።
የፓርቲዎች ቁጥር እስከ 74 ደርሶ እንደነበርና በዳግም ምዝገባ ሂደቱ ውስጥ በርካቶች በመቀነሳቸው አሁን ላይ 65 ያህል ሆነዋል ሲሉ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ ነግረውናል። በፓርቲዎች መካከል ልዩነቶቻቸውን ከሀገራዊ ጥቅም አንጻር ለምፍታትና ለማቀራረብ ከስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ቀደም ብሎ የተጀመረ ቢሆንም በምርጫውና በልዩ ልዩ ምክንያቶች ሳይጠናቀቅ ተገፍቶ እስከዛሬ ደርሷል ይሉና አሁን በማያግባቧቸው ጉዳዮች መካከል ምርጫቦርድ ባለበት ውይይት ማድረጋቸውን አቶ ውብሸት ገልጸዋል። መሰል ውይይቶች በፓርቲዎች መካከል አንድነትና ቅንጅት በመፍጠር አለመተማመንንም የሚያከስም ነው ሲሉም ያክላሉ።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ሰፊ ልዩነት በመኖሩ ምክንያት ቅርርብና ምክክር ያስፈልጋል በሚል ሲጠይቁ የነበረው ከ20 አመታት በፊት መሆኑንና የወቅቱ መንግስት ምክክሩን ስላላመነበትና ስላጣጣለው የዘገየ ጉዳይ መሆኑን የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ፖለቲካ ፓርቲ ፕሬዝደንት አቶ ማሙሸት አማረ ይናገራሉ። ነገር ግን አሁን ላይ ቢዘገይም ወደ ምክክር መመጣቱና የፓርቲዎች ምክክርም ይጠቅማል ተብሎ በአጀንዳነት ለምክክር ኮሚሽኑ የሚቀርብ ከሆነ ለዘርፉ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ጠቃሚ ነው ብለዋል። በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አሰባሳቢነት በጋራ የተደረገው የፓርቲዎች ውይይት ወሳኝ የሚባሉ ነጥቦችን በጋራ ማንሳቱን በማውሳት ለየግል ፓርቲዎች ከጠየቁት ጥያቄ ውጭ ይሄኛው አጋጣሚ ፓርቲዎቹ የጋራ አንድ የሚያደርጋቸውን ነጥብ የለዩበት ሆኖ አልፏል ሲሉ አቶ ማሙሸት ገልጸዋል። በመሆኑም መሰል የጋራ የፓርቲዎች ለምክክር ኮሚሽኑን ስራ ያቀለሉ እንደሚሆኑ ይታመናል ብለዋል።
ምክክር ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት 2014 ዓ.ም ጊዜ አንስቶ የበርካቶችን አጀንዳ ልየታና ስብሰባ ሲያደርግ መቆየቱን ሲናገር ቆይቷል። ኮሚሽኑ ሲቋቋም እንደ ርዕይ ብሎ ያስቀመጠው እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሀገራዊ መግባባት ተፈጥሮ ማየት የሚል ነው። እንዲሁም በአላማነት ከዘረዘራቸው ጉዳዮች መካከል ለአገራዊ መግባባት እና ጠንካራ ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ጽኑ መሠረት መጣል የሚለው ይገኝበታል። በመሆኑም ይህንን የመሰለ ርዕይና አላማ ሰንቆ የተነሳ ምክክር ኮሚሽን አሁን ላይ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ውይይት ሳያከናውንና በተለይም የተአማኒነትና የገለልተኝነት ጥያቄዎች እየተነሱበት ቀጥሏል።
በዚሁ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ በያዝነው 2017 ዓ.ም ውስጥ ሁሉንም አካላት አናግሮና አጀንዳቸውን ሰብስቦ ተልእኮውን ይጨርሳል ቢባልም በርካታ አካላትንና አካባቢዎች ያላደረሰ በመሆኑ ባለፉት ሳምንታት ዋና ኮሚሽነሩ ለኮሚሽኑ ስራ መሳካት ይረዳ ዘንድ ተጨማሪ ቀናት እንደሚያስፈልግ መናገራቸው ተሰምቷል። ለመሆኑ ቀናቶች ቢጨመሩስ ከቀጣዩ ምርጫ በፊት ኮሚሽኑ ራእዩን አሳክቶ ይጨርሳል ወይ የሚለው ዛሬም የብዙዎች ጥያቄ ሆኖ ቀጥሏል።
ምላሽ ይስጡ