✅የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ራሳቸውን ከተሳትፎ ያገለሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አጀንዳቸውን እንዲያቀርቡ ጥሪ ማቅረቤን እቀጥላለሁ ብሏል፤ፓርቲዎች በበኩላቸው ያስቀመጧቸው ቅደመ ሁኔታዎች እስካልተሟሉ ድረስ እንደማይሳተፉ በድጋሚ ገልጸዋል፡፡
✅በሌላ በኩል እስካሁን የተሰበሰበው አጀንዳ በቂ በመሆኑ የፓርቲዎች አለመሳተፍ የምክክሩ ስራ ምሉዕነት ላይ ተጽዕኖ አይፈጥርም ተብሏል፡፡
ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ አገራዊ ምክክር ለማድረግ በተለያዩ ክልሎች የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ እያከናወነች ትገኛለች፡፡ ከትግራይ እና አማራ ክልሎች ውጪ በሌሎቹ 10ሩም ክልሎች እና ሁለቱ ከተማ መስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰቡ ስራ ተጠናቋል፡፡
አገራዊ ምክክር የሚደረገው እንደ አገር ያላግባቡ፤ ለግጭትና ጦርነት የሚጋብዙ የማያሻግሩ የተባሉ ጥያቄዎችን ለይቶ በማውጣት፤ በጉዳዩ ዙሪያ በመምከር መግባባት ላይ ለመድረስ በማሰብ ነው፡፡
እንደ አለም አቀፍ የህግ ባለሙያው አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ ማብራሪያ አገራት ከጦርነት በኃላ፤ አሊያም ወደ ጦርነት የሚያስገባ ትልቅ አገራዊ ቀውስ ሲያጋጥማቸው ቀውሱን ለማስቀረት እና ችግሩን በዘላቂነት በሰላም ለመፍታት አገራዊ ምክክር ያደርጋሉ፡፡
እ.ኤአ. በ1994 በአጭር ጊዜ ውስጥ የ800ሺ ዜጎችን ህይወት የቀጠፈውን የሩዋንዳ የእርስ በእርስ የዘር ፍጅት ተከትሎ አገራዊ ምክክር በመደረጉና ችግሩም በዘላቂነት በመፍታቱ አገሪቱ አሁን ላይ በአፍሪካ ሰላማዊ፤ የተረጋጋች እና ዜጎች የተሻለ ህይወት የሚኖሩባት ተመራጭ አድርጓታል ይላሉ የህግ ባለሙያው፡፡
በኢትዮጵያም ለዘመናት እየተንከባለሉ መጥተዋል፤ እንደ ህዝብ በአብሮነት ለመቀጠል እንቅፋት ይሆናሉ፤ ብሔራዊ አለመግባባትን የፈጠሩ ጉዳዮች ናቸው የተባሉትን አጀንዳዎች በመለየት በጉዳዩም ዙሪያ ተወያይቶ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ የሚያስችል አገራዊ የምክክር ኮምሽን በ2014 ዓ/ም ተቋቁሞ የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራውን እያከናወነ እንዳለ ይታወቃል፡፡
በአገራዊ ምክክሩ ጥቂት የማይባሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸውን ከተሳትፎ ማግለላቸው የሚታወቅ ነው፡፡ የሀሳብ ልዩነት አለን ለኢትዮጵያ እና ለህዝቡ የሚበጀው ይህ ነው ብለው የፖለቲካ ርዕዩት ዓለማቸውን አንግበው በህጋዊነት የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች በአገራዊ ምክክሩ አለመሳተፋቸው እና አጀንዳቸውን አለማቅረባቸው በምክክሩ ስራ ምሉዕነት ላይ ምን ተጽዕኖ ይፈጥር ይሆን የሚለውን በርካቶች ይጠይቃሉ፡፡
ራሳቸውን ከተሳትፎው ካገለሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ ፓርቲ /ኦፌኮ/ ነው፡፡
የፓርቲው ጸሐፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ ፓርቲያቸው አሁንም በአገራዊ የምክክር ኮምሽኑ ስራ የመሳተፍ ፍላጎት እንደሌለው፤ የገለልተኝነት ጥያቄያቸው እንዳልተፈታ ለመናኸሪያ ራዲዮ አስታውቀዋል፡፡
በአዲስ አበባ፤ በኦሮሚያ ክልል ብሎም በሌሎችም አከባቢዎች ዜጎች ተሰባስበው መወያየታቸው አጀንዳ ማሰባሰባቸው ተገቢ እንደሆነ የገለጹት አቶ ጥሩነህ፤ ፓርቲያቸው ባይሳተፍበትም ምክክሩ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስብራት ከጠገነ በቂ ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡
ኮምሽኑ እንደ አገር የተስፋፋውን የሙስና ችግር፤ የመልካም አስተዳደር እጦት፤ የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ችግር እና የሰላም እጦትን የሚፈታ ከሆነ ገዢው ፓርቲም ይህንን ተቀብሎ ለማስተግበር ቁርጠኝነት ካለው በምክክሩ የፓርቲያቸው መሳተፍ አለመሳተፍ ትኩረት የሚስብ ጉዳይ ሊሆን አይገባም ብለዋል፡፡ እንደ ፓርቲ ኦፌኮ ግን በገዢው ፓርቲ እና በኮምሽኑም ላይ ጥያቄ እንዳለው ነው ያመላከቱት፡፡
አቶ ጥሩነህ በምክክሩ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስብራት የሚጠግን ስራ በቁርጠኝነት የሚሰራ ከሆነ አፌኮ ወደ ፊት በምክክሩ ሊሳተፍ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተው፤ ባይሳተፍ እንኳን በኢትዮጵያ የተሟላ ሰላም፤ መልካም አስተዳደር እና ዲሞክራሲ ከሰፈነ ፓርቲው በደስታ ይቀበላል ብለዋል፡፡
የእናት ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ጌትነት ወርቁ በበኩላቸው ፓርቲያቸው ከዚህ ቀደም በአገራዊ የምክክር ኮምሽኑ ለመሳተፍ አስቀምጦት የነበረው ቅድመ ሁኔታ ባለመከበሩ በድጋሚ የመሳተፍ እቅድ እንደሌለው አስታውቋል፡፡
ለምክክሩ ግብዓት የሚሆኑ አጀንዳዎችን የሚያቀብሉ አንዳንድ ምሁራን እና ፖለቲከኞች የሚሳተፉበት እድል ባልተመቻቸበት መሳተፉ ምክክሩን ምሉዕ እንደማያደርገው ነው የገለጹት፤ ፓርቲውም በዚህ ምክንያት እንደማይሳተፍ በድጋሚ ገልጸዋል፡፡
በቅርቡም በአማራ ክልል በሚደረገው የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ እንድንሳተፍ ተጋብዘናል፤ ይህንን ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ ስለሌለ ከተሳትፎ ራሳችንን እንዳገለልን ነን ሲሉ ለመናኸሪያ ራዲዮ አስረድተዋል፡፡
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ ፓርቲ ጸሐፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ ኦፌኮን ጨምሮ ሌሎች ፓርቲዎች እና አባላቱ በአገራዊ ምክክር ኮምሽኑ ስራ አለመሳተፍ እንደ ሀገር በምክክሩ ስራ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ እንደሚፈጥር ነው የተናገሩት፡፡
አንዳንድ ፓርቲዎቹ ምክንያት ጠቅሰው ራሳቸውን ቢያገሉም መፍትኤ የሰጣቸው አካል የለም ብለዋል፡፡ በቅርበት መመካከር ሳይሆን በርቀት መተያየት ነው ያለው፤ አግላይ የፖለቲካ ስርዓትን ነው የምንከተለው ሲሉ የፖለቲካ ስርዓቱንም ተችተዋል፡፡
አለም አቀፍ የህግ ባለሙያው አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ በበኩላቸው በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 ለ3 ዓመት የሥራ ዘመን ቆይታ የተቋቋመው አገራዊ የምክክር ኮምሽን ለሁሉም ተሳታፊዎች፤ እንዲሳተፉ እድል መፍጠር ቀጥተኛ ኃላፊነት እና ተልዕኮው እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
እድሉ ተፈጥሮላቸው ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች የማይሳተፉ፤ ያኮረፉ፤ ራሳቸውን ያገለሉ አካላት በምክክሩ አለመሳተፋቸው የሚያጎለው ነገር አይኖርም፤ እስካሁን እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል በቂ የሚባሉ አጀንዳዎች እንደተሰበሰቡ መረጃው አለኝ ብለዋል፡፡
ራሳቸውን ያገለሉ አካላት በምክክሩ ቢሳተፉ መልካም ነበር ነገር ግን አለመሳተፋቸው ያን ያህል በአገራዊ የምክክሩ ስራ ላይ ጉድለት ካለመፍጠርም ባለፈ የምሉዕነት ጥያቄ እንደማያስነሳ የህግ ባለሙያው አስረድተዋል፡፡
ዛሬም ድረስ ላለፉት 30 ዓመታት ስንገለገልበት በቆየነው የኢፌድሪ ህገ-መንግስት ረቂቅ ላይ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት አለመሳተፋቸውን በምሳሌነት በመጥቀስ የሁሉም አካላት አለመሳተፍ ያን ያህል የሚያጎለው ነገር አለመኖሩን በንጽጽር አብራርተዋል፡፡
የህግ ባለሙያው ማኩረፍ እና ከተሳትፎ ራስን ማግለል ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓት እና አገራዊ ጉዞ ጥቅም እንደሌለው ነው የሚገልጹት፤ በአገራችን ዛሬም ድረስ የሰለጠነ የፖለቲካ ስርዓት መገንባት ያልተቻለውም መመካከርን ባህል ባለማድረጋችን፤ ችግሮችን በንግግር የመፍታት ልምድ ባለማዳበራችን እና በአኩራፊነታችን ምክንያት ነው ይላሉ፡፡
በኦሮሚያ ክልል ደረጃ በአገራዊ ምክክሩ አጀንዳ የማሰባሰብ ሒደት ሲሳተፉ አግኝተን ያነጋገርናቸው ከእምነት ተቋም የተወከሉት የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያናት ህብረት የቦርድ ሰብሳቢ ፓስተር ደሳለኝ አበበ በኢትዮጵያ አሁን ላይ ያሉ መሰረታዊ ችግሮችን ለመፍታት ምክክር ብቸኛ እና ሰላማዊው አማራጭ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲሳካላቸው ሲያሸንፉ፤ በህዝብ ቅቡልነትን ሲያገኙ አገር እና ህዝብ የማስተዳደርና የመምራት ግብ ያላቸው እንደመሆኑ መጠን በምክክሩ ሒደት በመሳተፍ በሰላማዊ መልኩ አጀንዳቸውን ማቅረቡ ተገቢ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ለዘመናት በኢትዮጵያ ሲስተዋል የቆየው በአገራዊ ጉዳይ ከመሳተፍ ይልቅ የማግለል እና የማኩረፍ አባዜ ህዝብንም አገርንም ብዙ መስዕዋት አስከፍሏል ያሉት የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያናት ህብረት የቦርድ ሰብሳቢው ፓስተር ደሳለኝ፤ ሀሳብን ለምክክር ማቅረብ ለአገር እና ለህዝብ የሚኖረው ጠቀሜታ የጎላ ነው ብለዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ነፍጥ አንግበው ጫካ የገቡ አካላትን በማግባባት በሰላማዊ መልኩ የልዩነት ሀሳባቸውን አቅርበው ከስምምነት እንዲደርሱ ሰላማዊ ትግል እንዲደረግ የማግባባት፤ በባህላዊ መልኩ የማሸማገል ስራ ከሚሰሩ አካላት መካከል አባገዳዎች እና ሀደሲንቄዎች ከፍተኛውን ሚና እየተወጡ እንዳለ ይታወቃል፡፡
የገዳ ስርዓት ገደብ የሌለው የዲሞክራሲ ስርዓት ነው የሚሉት አባገዳ ቃሲም ሁሴን፤ ከሰሞኑን በጃል ሰኚ ነጋሳ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አባላት እና አመራር ከመንግስት ጋር እንዲቀራረብ እንዲሁም ፖለቲካዊ ችግራቸውን እና ልዩነታቸውን በሰላማዊ መልኩ እንዲፈቱ የማግባባትና የማነጋገር ስራን ባህላዊ ስርዓቱን በተከተለ መልኩ መሰራቱን እና ውጤትም ማምጣቱን አስታውሰዋል፡፡
በኦሮሞ ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው ስርዓቱም ሆነ አባገዳዎች ህዝባዊ ችግሮች እና ጥያቄዎች በሰላማዊ መልኩ እንዲፈቱ የማግባባቱን ስራ መስራታቸውን እንደሚቀጥሉም ነው ያመላከቱት፡፡
በአገራዊ የምክክር ኮምሽኑ ስራም በተለያዩ ምክንያቶች ራሳቸውን ያገለሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምክክሩ ሒደት እንዲሳተፉ የማግባባት ስራ ከመስራት ባለፈ በቅድመ ሁኔታ መልክ የቀረቡ መስተካከል የሚችሉ ጉዳዮችን መፍታት እና ማስተካከል እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ አባገዳዎች የተኳረፉ ቡድኖችን የማግባባቱን፤ ለንግግር የማቀራረቡን ስራ እንዲሰሩ መንግስት እንዲያግዛቸው ጠይቀዋል፡፡
ያኮረፉ እና ራሳቸውን ከተሳትፎ ያገለሉ አካላት ወደ አባገዳዎች፤ የሀገር ሽማግሌዎች በመቅረብ ጥያቄዎቻቸው ምላሽ እንዲያገኝ የመወትወት ስራ መስራት እንደሚገባቸው የተናገሩት አባገዳ ቃሲም ሁሴን መንግስትም ይህንን ስራ በኃላፊነት ማከናወን አለበት ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የአገራዊ የምክክሩ ስራ የተሳካ እና ውጤታማ እንዲሆን አባገዳዎች ኮምሽኑ ከመቋቋሙ ቀደም ብሎ ሲሰሩ ነበር ያሉት አባገዳ ቃሲም፤ እንደ ኦሮሚያ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር ሰላማዊ የንግግር እና ምክክር ሒደት እንዲሰፍን ኦሮ- አማራ በሚል የጋራ መግባባት እና አንድነት እንዲሰፍን ሰፊ ስራ መሰራቱን፤ አሁንም ነፍጥ አንግበው ጫካ የገቡ አካላት በሰላማዊ ንግግር እና ውይይት ጥያቄያቸውን እዲፈቱ የማሸማገሉ ስራ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
መናኸሪያ ራዲዮም ጥቂት የማይባሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮምሽን እያካሔደ ካለው አጀንዳ የማሰባሰብ እና የምክክር ስራ ራሳቸውን እንደማግለላቸው፤ ኮምሽኑ እነርሱን በድጋሚ ለማሳተፍ ምን የተለየ ስልት ነድፏል፤ ምንስ አቅዷል ሲል ጠይቋል፡፡
የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮምሽን ኮምሽነር አምባሳደር መሐመድ ድሪር ኮምሽኑ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ታጣቂ ኃይላት፤ ማንኛውም አጀንዳ አለኝ የሚል ግለሰብም ሆነ ቡድን አጀንዳውን እንዲያቀርብ፤ በሒደቱም እንዲሳተፉ ኮምሽኑ አስቻይ ሁኔታዎችን እንዳመቻቸ ወደፊትም ይህንኑ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
የሰላም አማራጭን ፈልገው ህዝቡን የተቀላቀሉ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አባላትም በአጀንዳ ማሰባሰብ ሒደቱ እንደተሳተፉ ነው ኮምሽነር አምባሳደር መሐመድ ድሪር ያብራሩት፡፡
ኮምሽነሩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አለኝ የሚሉትን የፖለቲካ አጀንዳቸውን እንዲያቀርቡ ኮምሽኑ ጥሪውን ማቅረቡን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
እንደ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አባላት ሁሉ ሌሎችም ታጣቂ ኃይላት በሰላማዊ አማራጭ ትግል ማድረግን እንደሚመርጡ፤ በአገራዊ የምክክር ኮምሽኑም ስራ እንደሚደሳተፉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ ዓመት አገራዊ ምርጫ በሚጠበቅበት በዚህ ወቅት፤ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ዜጎችን ያላግባቡ በጋራም በአብሮነት በሰላም ለመቀጠል እንቅፋት ይፈጥራሉ፤ በውይይት እና በሰላማዊ ምክክር የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ያስፈልጋል በሚል ሐገራዊ ምክክር ለማከናወን የአጀንዳ ማሰባሰቡ ስራ እየተጠናቀቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡
ኮምሽኑ በኢትዮጵያ መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ አጀንዳዎች ላይ ሀገራዊ ምክክሮችን በማካሄድ፣ ምክረ ሀሳቦችን በማቅረብ እና ለተግባራዊነቱም የመከታተያ ስርዓት በመዘርጋት ለሀገራዊ መግባባት ምቹ ሁኔታ መፍጠር ዋነኛ ተልዕኮው እንደሆነም ይታወቃል፡፡
ምላሽ ይስጡ