ኅዳር 30 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) መንግስት የሃገሪቱን ሰላም ለማረጋገጥ ከታጣቂዎች ጋር የተለያዩ የሰላም ስምምነቶችን እያደረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሰላማዊ ስምምነትን የሚቀበሉ ታጣቂዎች ወደ ማህበረሰቡ ከመቀላቀላቸው በፊት ወደ ተሃድሶ ማዕከላት ገብተው የተለያዩ ስልጠናዎችን የሚወስዱበት ሂደት መኖሩ ይታወቃል፡፡
ይህንንም ተከትሎ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ይህንን ስምምነት በመቀበል ወደ ተሃድሶ ማዕከል እየገቡ ያሉ በርካታ ታጣቂዎች መኖራቸው እየተገለጸ ይገኛል፡፡
ባሳለፍነዉ እሁድ እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራዉ ቡድን ጋር የሰላም ስምምነት መፈጸሙን ተከትሎ ታጣቂዎች ወደ ተሃድሶ ማዕከላት ሲጓዙ በመዲናዋ ከፍተኛ የተኩስ ድምፅ ሲያሰሙ እንደነበረ ፤ይህ ደግሞ በከተማው ነዋሪ ላይ ከፍተኛ ድንጋጤና መረበሽ እንዲፈጠር በማድረጉ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ይቅርታ መጠየቁ ይታወቃል፡፡
ይህንን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መግለጫ ያወጣ ሲሆን የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ እዩኤል ሰለሞን ለመናኸሪያ ሬዲዮ እንደገለፁት ማንኛውም የሰላም ስምምነት ተቀብሎ የሚገባ ታጣቂ ቡድን በቅድሚያ መሳሪያውን አስረክቦ ሊሆን እንደሚገባ በመጥቀስ በከተማዋ የተፈጠረው ድርጊት ግን ህዝቡን እንዲረበሽ እና ድንጋጤ ውስጥ እንዲገባ ያደረገ ድርጊት ነው ብለዋል፡፡
የሰላም ስምምነት እና በጠረጴዛ ዙሪያ ንግግር መካሄድ ለሀገራችን እጅግ ወሳኝ እና ተቀባይነት ያለው ሃሳብ ቢሆንም በሰላም ስምምነቱ መሰረት እየገቡ ካሉ ታጣቂ ሀይሎች ጋር ያለውን ስምምነት ቅርፅ እና ይዘት መንግስት ለህዝቡ ግልጽ ሊያደርግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም የሰላም ስምምነቱ የአለም አቀፍ መርሆችንም የተከተለ ሊሆን የሚገባ እንደመሆኑ መሳሪያ ማስረከባችዉ ቀዳሚ ተግባር ነዉ ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደምም በሌሎች አካባቢዎችም መሰል ድርጊት እንደማጋጠሙ በዜጎች ላይ ጥቃት እንዳይደርስ ትምህርት ሊወሰድ እንደሚገባ አፅንዖት ሰጥተውበታል፡፡
የህግ ባለሙያው አቶ ዮናስ ወልደየስ፤ ወደ ተሃድሶ የሚገቡ ታጣቂዎችን በሚመለከት በቅድሚያ ከሚደረጉ ተግባራት መካከል መሳሪያ ማስረከብም እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ መሳሪያ ለደስታ በሚል እንኳን የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች በየትኛውም አግባብ መተኮስ በህግ ተጠያቂ የሚደርግ እና የተከለከለ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ታጣቂዎቹ ለደስታ በሚል ያደረጉት ተግባር ማህበረሰቡንም ሆነ የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች ላይ ድንጋጤን የሚፈጥር እንዲሁም ጉዳት እንዲደርስ የሚያደርግ ድርጊት ነው ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ጉዳዩን አስመልከቶ ባወጣው መግለጫ ታጣቂዎቹ ወደ ተሃድሶ ማዕከላት እየተጓዙ መሆኑን እና ለደስታ በሚል የፈጸሙት ድርጊት መሆኑን በመጥቀስ ለተፈጠረው ድርጊት ይቅርታን ጠይቋል፡፡መሰል ድርጊቶች በድጋሚ እንዳይፈጠሩ ታጣቂዎችን ትጥቅ ቅድሚያ ማስፈታት ላይ ሊሰራ እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
መናኸሪያ ሬዲዮ 99.1
ሃሳብ፣አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት የሚከተሉትን የስቱዲዮ ስልኮቻችን ይጠቀሙ
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
የቀጥታ ስርጭት 👉 📻 (https://worldradiomap.com/et/play/menaharia) radio 99.1 (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
✅ Telegram (https://t.me/menaharia_fm)
ትክክለኛውን የመናኸሪያ ሬዲዮ የዩቱዩብ አድራሻ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
➲ Youtube (https://www.youtube.com/channel/UC8uROsU69D8Ob65XapeHvIw)
ምላሽ ይስጡ