ኅዳር 27 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) በኦሮሚያ ክልል የተጀመሩ የሠላም ንግግሮች በሌሎች የሀገሪቷ አካባቢዎችም ተግባራዊ መሆን እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡ የስነ አመራር መምህር እና የፖለቲካ ባለሙያው አቶ ጌትዬ ትርፌ በኦሮሚያ ክልል ከሰሞኑ የተደረገው የሰላም ስምምነት ተስፋ ሰጭ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ጫካ ከቀረው ሌላኛው የሸኔ ክንፍ ጋር አሁንም ንግግሮች እና ድርድሮች መቀጠል እንዳለባቸው ነው ያመላከቱት፡፡ የተጀመሩ ንግግሮች ውጤት እንዲያመጡ ከፖለቲከኞች፤ በትጥቅ ትግል ላይ ከሚገኙ አካላት፤ ከማህበረሰቡም ሆነ ከመገናኛ ብዙሃን ከፍተኛ ስራ እንደሚጠይቅ ያመላከቱት ባለሙያው፤ የአንድ ወገን ልፋትና ስራ ብቻውን ውጤት ሊያስገኝ አይችልም ብለዋል፡፡
በቀጣይ በሚደረጉ ንግግሮች እና ውይይቶች በመንግስት ሹመኞች በኩል የሚደረጉ ንግግሮች ጥላ እንዳያጠላባቸው ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ መደረግ እንደሚገባውና ትልቁን ስራ መንግስት መስራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ በአማራ ክልል የሚገኙ በትጥቅ ትግል ላይ የሚገኙ ወገኖችም ቢሆኑ በኦሮሚያ ክልል ከተደረገውን የሠላም ስምምነት ትምህርት መውሰድ እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል ያለው ግጭት እንዲባባስና ሠላም እንዳይሰፍን እያደረጉ የሚገኙ አካላት ከድርጊታቸው ተቆጥበው በትጥቅ ትግል ላይ የሚገኙ አካላት ወደ ሠላም እንዲመጡ ሁሉም አካላት ርብርብ ማድረግ እንደሚገባቸው ነው ባለሙያው ያመላከቱት፡፡ ሀገሪቷ ግጭት ውስጥ በቆየች ቁጥር ለውጭ ተጽዕኖ ተጋላጭነቷ እየጨመረ ስለሚሄድ የጸጥታውን ችግር በአስቸኳይ መፍታት ይገባል ብለዋል፡፡
መንግስት በአማራ ክልል ያለውን ግጭት በሠላማዊ መንገድ እልባት እንዲያገኝ እየሰራ መሆኑን የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ተናግረዋል፡፡ ከሰሞኑ በተለያዩ የሀገሪቷ አከባቢዎች በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ ታጣቂዎች የቀረበውን የሠላም ጥሪ ተቀብለው እየተመለሱ ይገኛሉም ብለዋል፡፡
ፊልድ ማርሻሉ በኦሮሚያ ክልል መንግስት እና የሠላም ጥሪን ተቀብለው ከገቡ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ጋር የሠላም ስምምነት በተደረገበት መድረክ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር መንግስት በሁሉም አካባቢ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት ወደ ሠላም እንዲመለሱ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በዚህም አሁን ላይ በአማራ ክልል ያለውን ግጭት ለማስቆም እና ወደ ሠላም ንግግር ለመመለስ ስራዎች እየተሰሩ እንዳሉ፤ በቅርቡ እውን ይሆናል የሚል ግምት እንዳላቸው አመላክተዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል እና በሌሎች አካባቢዎች ለታየው አንጻራዊ ሠላም መከላከያ ሠራዊቱ ሚናው የጎላ እንደነበር የገለጹት ፊልድ ማርሻሉ፤ እንደ ሀገር የተወጠኑ እቅዶች ዳር እንዲደርሱ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
መናኸሪያ ሬዲዮ 99.1
ሃሳብ፣አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት የሚከተሉትን የስቱዲዮ ስልኮቻችን ይጠቀሙ
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
የቀጥታ ስርጭት 👉 📻 (https://worldradiomap.com/et/play/menaharia) radio 99.1 (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
✅ Telegram (https://t.me/menaharia_fm)
ትክክለኛውን የመናኸሪያ ሬዲዮ የዩቱዩብ አድራሻ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
➲ Youtube (https://www.youtube.com/channel/UC8uROsU69D8Ob65XapeHvIw)
ምላሽ ይስጡ