ኅዳር 23 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) ባለፉት 5 ዓመታት ሀገር ውስጥ ያሉ ግጨቶችና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መቀያየር ተቋሙ ውጤታማ እንዳይሆን እንዳደረገው ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስተያየታቸው የሰጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ 5ተኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ባከበረበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባለፉት ጊዜያት የተሻለ ውጤት የተገኘበት እንደነበር ተናግረዋል።
በእነዚህ ጊዜያት ኢትዮጵያ ከቃላት መወራወር ባለፈ ከአንድም ጎረቤት አገር ጋር ጦር አለመማዘዟን ገልጸዋል። መናኸሪያ ሬዲዮም ያነጋገራቸው ባለሙያዎች ያለፉት 5 ዓመታት በስኬት ብቻ የሚነሱ አለመሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የመጀመሪያዎቹ ሁለት አመታት የተሻለ የዲፕሎማሲ ውጤቶች የተስተዋሉበት እንደነበር፣ ነገር ግን በጥቅሉ በአምስቱ አመታት ግን ዲፕሎማሲው የተዳከመበት ጊዜ እንደነበር የተናገሩት በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ዶክተር ደጉ አስረስ ናቸው፡፡
ባለፉት አምስት አመታት በዲፕሎማሲው መስክ እንደ ስኬት ከሚነሱ ጉዳዮች ኢትዮጵያ የብሪክስ ትብብር ማዕቀፍ አባል የሆነችበት ዋነኛው መሆኑን ነገር ግን እሱም ቢሆን በቀጣይ እንደ ሀገር ምን ውጤት አስገኘልን የሚለው ተግምግሞ መታየት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ስኬታማ እንዳትሆን ያደረጋት ሁለት ምክንያቶች ናቸው ያሉት ዶክተር ደጉ አስረስ፣ አንደኛው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በፍጥነት መቀያየር ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በሀገር ውስጥ ያሉ ግጭቶች ናቸው ብለዋል።
በዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲ እና የውጭ ግንኙነት ፖሊስ መምህር አቶ አበራ ሄብሶ በበኩላቸው ባለፉት አምስት አመታት በዲፕሎማሲው ረገድ የተሰሩ ስራዎች አበረታችና ዘላቂ ጥቅምን ከማስጠበቅ አንፃር ውጤታማ እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የተደረገው ድርድር ያስገኘውን ውጤት ለአብነትም ጠቅሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ተቋሙን በማብቃት ረገድ ብዙ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው ነው የተናገሩት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቀጣይ አመታት በዲፕሎማሲው ረገድ የጎረቤት ሀገራትን ጥቅም ያስቀደመ ትብብርን መሰረት ያደረጉ ስራዎች እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
መናኸሪያ ሬዲዮ 99.1
ሃሳብ፣አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት የሚከተሉትን የስቱዲዮ ስልኮቻችን ይጠቀሙ
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
የቀጥታ ስርጭት 👉 📻 (https://worldradiomap.com/et/play/menaharia) radio 99.1 (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
✅ Telegram (https://t.me/menaharia_fm)
ትክክለኛውን የመናኸሪያ ሬዲዮ የዩቱዩብ አድራሻ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
➲ Youtube (https://www.youtube.com/channel/UC8uROsU69D8Ob65XapeHvIw)
ምላሽ ይስጡ