ኅዳር 17 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ጣቢያዎች በተለያዩ የሙያ ዘርፍ ላይ ያሉ ነገር ግን ፍላጎት ያላቸዉ ሙያተኞችን እንደሚቀጥሩ ይታወቃል፡፡ ይህ አሰራር አንድም ከፍተኛ ክህሎት ያላቸዉ ሙያተኞችን እያወጣ ቢሆንም በተቃራኒዉ ደግሞ ሙያዊ አሰራር እና መርሆች እንዲጣሱ እያደረገ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ ይህ ችግር በስፋት የሚስተዋለዉ ደግሞ ታዋቂነትን ብቻ መሰረት ያደረጉ የጋዜጠኝነት የስራ ቅጥሮች መፈጸማቸዉ እንደሆነ ይነሳል፡፡
ሚዲያዎች አሁን ላይ ታዋቂነትን መሰረት ያደረጉ ቅጥሮችን መፈጸማቸዉ መሰረታዊ ከሚባለዉ የጋዜጠኝነት ሙያዊ ሃላፊነት በተጨማሪ ከፍተኛ ሙያዊ አሰራሮችና መርሆዎች እንዲጣሱ እያደረገው መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎችና የሚዲያ የስራ ኃላፊዎች ለመናኸሪያ ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 ሬዲዮ ጣቢያ ዋና ስራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ መሰለ ገብረሕይወት፤ ሙያው የሚገባውን ያህል ትኩረት ባለ ማገኘቱ ጠንካራ ሙያተኛና ሚዲያ በሀገሪቷ ውስጥ በስፋት እንዳይፈራ አድርጓል ያለ ሲሆን በመንግስት በኩልም ይህ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ትኩረት የተነፈገዉ በመሆኑ ዘርፉ ላይ ችግሮች እንዲፈጠሩ አድርጓል፤ አሰራር እና ደንብ ሊበጅለት ይገባል ሲልም ገልጿል፡፡
በዲላ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ክፍል መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር አለበል ጓንጉል አሁን ላይ በስፋት ሚዲያዎች እየተከተሉት ያለው አሰራርና ቅጥር ሙያና ሙያተኛን መሰረት ያደረገ ሳይሆን ታዋቂነትን መሰረት ያደረጉ በመሆናቸው ምክንያት የጋዜጠኝነት ሙያ አሰራርና መርህ እየተጣሰ ይገኛል ብለዋል፡፡
ይህ አሰራር ዘርፉን የሚጎዳ በመሆኑ ህጋዊ እና ሙያዊ እልባት ሊሰጠዉ ይገባል የሚል ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡
አዋጅ ቁጥር 1238/2013 መሰረት የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ለሚዲያዎች ፍቃድ የመስጠትና የቁጥጥር ስራዎች የመስራት እንዲሁም በዋናነት የይዘት ቁጥጥርና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንዲያደረግ ብቻ ተደርጎ መደንገጉ ሚዲያዎች በነፃነት የፈለጉትን ባለሙያ ቅጥር እንዲያደረጉ እንዳደረጋቸው ብሎም በሚሰሩ ዘገባዎች ውስጥም ሙያዊ ስነ ምግባር እንዲሸራረፍ እያደረገው መሆኑን ባለሙያዎቹ ጠቁመዋል፡፡
በአዋጅ ላይ የተሰጠዉ ስልጣን የስራ ቅጥር እና መርህን የተመለከተ ድንጋጌ የተመለከተ ባለመኖሩ ዘርፉ በዘፈቀደ ቅጥር የሚፈጸምበት እንዲሆን አድርጎታል ያሉት ባለሙያዎቹ ህጋዊ አሰራር እና ደንብ ሊበጅለት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
መናኸሪያ ሬዲዮ 99.1
ሃሳብ፣አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት የሚከተሉትን የስቱዲዮ ስልኮቻችን ይጠቀሙ
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
የቀጥታ ስርጭት 👉 📻 (https://worldradiomap.com/et/play/menaharia) radio 99.1 (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
✅ Telegram (https://t.me/menaharia_fm)
ትክክለኛውን የመናኸሪያ ሬዲዮ የዩቱዩብ አድራሻ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
➲ Youtube (https://www.youtube.com/channel/UC8uROsU69D8Ob65XapeHvIw)
ምላሽ ይስጡ