ኅዳር 12 ቀን 2017 (መናኸሪያ ሬዲዮ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 40ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ያሳለፋቸው ውሳኔዎቹም እንደሚከተሉት ቀርበዋል፡፡
1.በቅድሚያ ምክር ቤቱ የተወያየው የመካከለኛ ዘመን (2017-2021) የማክሮ ኢኮኖሚ እና ፊስካል ማዕቀፍ ላይ ነው፡፡ ማዕቀፉ በሁለተኛው ምዕራፍ ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ የሚከናወኑ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችንና የመንግስት የፊስካል ፖሊሲ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ለማድረግ እና ለ2017 የፌዴራል መንግስት ተጨማሪ በጀትና የወጪ አሸፋፈን ማስተካከያ መነሻ ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ተቃኝቶና ተሻሽሎ የቀረበ ነው፡፡ ምክር ቤቱም በማዕቀፉ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
2.በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው በፌዴራል መንግስት የተጨማሪ በጀት እና የወጪ አሸፋፈን ማስተካከያ አዋጅ ላይ ነው፡፡ የተጨማሪ በጀት እና የወጪ አሸፋፈን ማስተካከያው የተሻሻለውን የ2017-2021 የመካከለኛ ዘመን የማክሮ ኢኮኖሚ እና ፊስካል ማዕቀፍ ማስፈጸም በሚያስችል መልኩ የመንግስት የፋይናንስ አቅምና ተጠባቂ ገቢዎችን ታሳቢ በማድረግ፣ የተጨማሪ በጀት ታሳቢዎችንና የወጭ ታሳቢዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት ተዘጋጅቷል፡፡
በዚሁ መሰረት ለመደበኛ ወጪዎች እና የወጪ አሸፋፈን ለማስተካከል የሚውል 581, 982, 390,117 /አምስት መቶ ሰማንያ አንድ ቢሊዮን ዘጠኝ መቶ ሰማንያ ሁለት ሚሊዮን ሶስት መቶ ዘጠና ሺህ አንድ መቶ አስራ ሰባት ብር/ ተጨማሪ በጀት ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረበው የፌዴራል መንግስት የ2017 በጀት ዓመት የተጨማሪ በጀትና የወጪ ማስተካከያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
3.ከዚያም ምክር ቤቱ የተወያየው በኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሂሣብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው። ኢንስቲትዩቱ ብቁ እና ብዛት ያላቸውን ባለሙያዎች በማፍራት በመንግስት እና በግል ተቋማት የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀት እና አቀራረብ ሥርዓት በመዘርጋት ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚኖረው ነው፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ግብዓቶችን በማከል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
4.የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ረቂቅ አዋጅ ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየበት አጀንዳ ነው፡፡ ደረቅ ቆሻሻ በአካባቢ እና በሰዎች ደህንነትና ጤና ላይ እያስከተለ ያለውን ተፅእኖ እና ጉዳት ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንደሀገር ባለፉት አመታት ከጀመርናቸው የግሪን ሌጋሲ ስራችንና የኮሪደር ልማት ውጤታማና ዘላቂ ለማድረግ፣ በዜጎች ጤንነት የከተማ ውበት መጠበቅ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለውን ለአንድ ጊዜ ግልጋሎት የሚውሉ የፕላስቲክ ምርቶችን ወደ ሀገር እንዳይገቡ ክልከላ በማድረግ፣ ህብረተሰቡንና ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ የደረቅ ቆሻሻ አሰባሰብ፣ አጓጓዝ፣ አከመቻቸት፣ መልሶ መጠቀም፣ መልሶ ኡደት እና አወጋገድ ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ በማስፈለጉ አዋጁ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በአዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምፅ ወስኗል፡፡
5.ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየው የብሄራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን ማቋቋሚያ ደንብን ለማሻሻል በወጣ ደንብ ላይ ነው፡፡ ተቋሙ በህግ የተሰጠውን ተግባርና ሀላፊነት መወጣት እንዲችል ማቋቋሚያ ደንቡን ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ደንቡ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በደንቡ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ በፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
6.ከዚያም ምክር ቤቱ የተወያየው የውሃ አካል ዳርቻ አከላለል፣ ልማት፣ እንክብካቤ እና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ በሀገራችን በውሃ አካላት ዳርቻዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል እንዲቻል የውሃ አካላት ዳርቻ መከለልና በዘላቂነት ማልማት፣ መንከባከብና ጥበቃ ማድረግ የውሃ ስነ-ምህዳር አግልግሎትን ከማሻሻል ባሻገር ለአካባቢው ማህበረሰብ ተጨማሪ ማህራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን የሚያስገኝ በመሆኑ አዋጁ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል:: ምክር ቤቱም በአዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምፅ ወስኗል፡፡
- በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው የተቀናጀ ውሃ ሀብት አስተዳደር ማስፈጸሚያ የተፋሰሶች ከፍተኛ ምክር ቤት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ያላትን የገፀ ምድርና የከርሰ ምድር የውሃ ሀብት በፍትሃዊነትና በዘላቂነት መጠቀም እንድትችል የሚመለከታቸው አካላት የውሃ ሀብትን በጋራ ለማልማት፣ ለመጠቀም፣ ለመንከባከብ፣ ለመጠበቅ እና ለመቆጣጠር የሚያስችል የተቀናጀ ውሃ ሀብት አስተዳደርን በተፋሰስ ደረጃ ተግባራዊ በማድረግ ስትራቴጂካዊ አመራር መስጠት አስፈላጊ በመሆኑ ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በአዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምፅ ወስኗል፡፡
ምላሽ ይስጡ