ኅዳር 12 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) የህጻናት መብትን፤ ችግሮችን እና በህጻናት ልጆች ላይ ለሚከሰቱ ጥቃቶች እና መሰል በደሎችን ማስተጋባት እንዲችሉ በህጻናት የሚመሩ ፓርላማዎች አስፈላጊ መሆናቸው የሚታወቅ ነዉ፡፡
ይሁን እንጂ በህጻናት ፓርላማ ስር ታቅፈው የሚንቀሳቀሱ ህጻናት ለሚጠይቋቸው ጥያቄዎች አጥጋቢ ውጤቶች እያገኙ አለመሆናቸውን መናኸሪያ ሬዲዮ ያነጋገራቸው የአማራ፤የትግራይ እንዲሁም የድሬዳዋ የህጻናት ፓርላማ ተወካዮች አስታውቀዋል፡፡
የአማራ ክልላዊ መንግስት የህጻናት ፓርላማ ዋና ኮሚቴ ሰብሳቢ ዳግም ሸዋንግዛው አሁን ላይ በክልሉ እየታየ ያለው የሰላም እጦትን ተከትሎ በፈለጉት ልክ መራመድ እንዳልቻሉ ገልጿል፡፡
ለዚህም ባለፉት ጊዜያት በክልሉ በተከሰተው ጦርነት እና አሁንም ያለው የሰላም እጦትን ተከትሎ የትምህርት ተቋማት በመፍረሳቸው ምክንያት በርካታ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ውጪ መሆናቸውን አንስቷል፡፡ የክልሉ የህጻናት ፓርላማ አባላት በኩል በርካታ ጥያቄዎች ለሚመለከታቸው ተቋማት እየቀረበ ቢሆንም በሚመለከታቸው ተቋማት በኩል የሚሰጣቸው ግብረ መልስ አነስተኛ መሆኑን ገልጿል፡፡
የትግራይ ክልል የህጻናት ፓርላማ ዋና አፈ-ጉባዔ ሉዓም ካሳይ እንደምትለው ከሆነ ባለፉት ጊዜያት በክልሉ የነበረው ጦርነትን ተከትሎ በርካታ በህጻናቱ ስነ ልቦና ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖና ጠባሳ ጥሎ ማለፉን ተናግራለች፡፡
በክልሉ ያሉ የትምህርት ተቋማት የተፈናቃዮች ካንፕ በመሆን እያገለገሉ እንደሚገኙ ገልጻ፤ በክልሉ 52 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች ትምህርታቸውን መጀመር አለመቻላቸዉን ጠቁማለች፡፡
በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የህጻናት ፓርላማ ተጠሪ ዘካሪያ ከድር የህጻናት ፓርላማ አባላት እያነሳቸው ካሉ ጥያቄዎች ውስጥ የሴቶች ጥቃት እና በትምህርት ተቋማት ዙሪያ ያሉ አዋኪ ቤቶች መቀነስ የሚቻልበት የቁጥጥር ስራዎች እንደሰሩ መሆኑን ተናግሯል፡፡ በህጻናቱ በኩል የሚነሱ ጥያቀዎች ምላሽ እንዲያገኙ በማድረግ ሂደት ውስጥ መዘግየቶች እንደሚስተዋሉ አንስቶ እንዲታረም ጠይቋል፡፡
የኢፌዴሪ ሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በህጻናቱ ፓርላማ ዙሪያ የተነሱ ጥያቄዎች መፍታት የሚቻልበትን አካሄድ እንደሚፈጥር አስታውቋል፡፡ በትላንትናዉ እለት በአለም አቀፍ ደረጃ ለ35ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ19ኛ ጊዜ ተከብሮ በዋለዉ የህጻናት ቀን ላይ የህጻናት ፓርላማ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
መናኸሪያ ሬዲዮ 99.1
ሃሳብ፣አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት የሚከተሉትን የስቱዲዮ ስልኮቻችን ይጠቀሙ
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
የቀጥታ ስርጭት 👉 📻 (https://worldradiomap.com/et/play/menaharia) radio 99.1 (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
✅ Telegram (https://t.me/menaharia_fm)
ትክክለኛውን የመናኸሪያ ሬዲዮ የዩቱዩብ አድራሻ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
➲ Youtube (https://www.youtube.com/channel/UC8uROsU69D8Ob65XapeHvIw)
ምላሽ ይስጡ