ኅዳር 09 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ የፌደራል አጀንዳ መረጣና ምክክር ሊጀምር መሆኑን ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል።
ኮሚሽኑ በእስካሁኑ ሂደቱ በሰባት ክልሎችና በሁለት ከተማ መስተዳደሮች ስራውን እያጠናቀቀ መሆኑን በመግለጽ በቀጣይ በፌደራል ደረጃ ምክክር ማድረግ የኮሚሽኑ አንዱ የስራ እቅድ እንደሆነና በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ የፊደራል አጀንዳ ልየታና ምክክር ይደረጋል ሲሉ ዋና ኮሚሽነሩ ፕ/ር መስፍን አርአያ ለጣቢያችን ገልጸዋል።
በኦሮሚያ ክልል ለዋናው ጉባኤ ምክክር የሚሆኑ ሰዎችን በቀጣይ ሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ መምረጥ ልንጀምር ነው ያሉት ፕ/ር መስፍን ይሁን እንጂ በትግራይና በአማራ ክልል አሁንም ሁኔታዎች ካልተመቻቹ ምክክር ለማድረግ አስቸጋሪ ነው ብለዋል፡፡
ምክክር በሶስት መንገድ ይከናወናል ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ በግጭት ውስጥ ፣ ግጭት ከበረደ በኋላና አስቀድሞ ወደ ግጭት እንዳይገባ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ እንደሚደረግ የሌሎች ሀገራት ታሪክም ያስረዳል ሲሉ ገልጸዋል። በመሆኑም አሁን ላይ በግጭት ምክንያት ታጣቂ ሃይሎች ወዳሉበት አካባቢ ለመድረስ ጥረት እየተደረገ እንደሆነና ታጣቂ ሃይሎቹን ወደ መድረክ ለማምጣትም መገናኛ ብዙሃንን እንደ ዋነኛ መሳሪያ እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል።
አጀንዳ ልየታና ምክክር ባልተደረገባቸው በተለይ በአማራና ትግራይ ክልሎች ሁኔታዎች ተመቻችተው ኮሚሽኑ ስራውን መስራት እንዲችል ዋና ኮሚሽነሩ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ምላሽ ይስጡ