ኅዳር 09 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫነት ባሻገር፤ ተጨማሪ ግድቦችንና ሐይቆችን በመፍጠር በዓሳ ሃብት ላይም የመስራት ከፍተኛ እቅድ እንዳለ ይታወቃል፡፡
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ የዓሳ ሃብት ልማት ባለሙያው አቶ ሙሸን ፉፋ፤ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሚገኝበትን ጉባ ወረዳን ጨምሮ፤ ግድቡ በሚያዋስናቸው 4 ወረዳዎች ውስጥ 72 የዓሳ አስጋሪ ማህበራትን ማደራጀት መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በ72ቱ ማህበረት ውስጥ 500 የሚሆኑ ወጣቶች እንዳሉ ገልጸው፤ እንደ ክልል የሚስዋለውን የስራአጥ ቁጥርም እንደሚቀንሰው አክለዋል፡፡
አሁን ላይ ከ72ቱ የዓሳ አስጋሪ ማህበራት ውስጥ በተደራጀ ሁኔታ ወደ ስራ የገቡት 6ቱ ማህበራት ብቻ እንደሆኑ አመላክተው ሌሎችን ማህበራትም ወደ ስራ ለማስገባት ከዚህ በፊት ግብርና ሚኒስቴር የዓሳ ማስገሪያ መረብ ድጋፍ ያደረገ ቢሆንም አሁን ሌሎችን ማህበራትንም ወደ ስራ ለማስገባት የማጥመጃ መሳሪያዎችን የማሟላት የአቅም ውስንነት እንዳለ ገልጸዋለ፡፡
በክልሉም ሆነ እንደሃገር የዓሳ ሃብትን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራበት አመላክተው፤ ክልሉ የመጀመሪያው ተጠቃሚ ስለሆነ የዓሳ ምርቱ በሚጠበቀው ልክ እንዲሆንና በዘርፉ በርካታ ወጣቶችን በስራው ለማሰማራት የአካባቢውን ስነ-ምህዳር መጠበቅና ከሚፈቀደው ውጭ ለማስገር የሚሞክሩትንም ጥብቅ የሆነ ክትትል እንደሚደረግ አመላክተዋል፡፡
ባለሙያው አክለውም በግብርና ሚንስቴር በኩል በተለይ በግድቡና በዓሳ ሃብቱ ዙሪያ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመሆን ጥናት ማድረግ እንደሚያስፈልግም አቶ ሙሸን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያላትን የዉሃ ሃብት ተጠቅማ በአሳ ሃብት ላይ መስስት እንደሚገባት እና አንዱም የህዳሴዉ ግድብ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ምላሽ ይስጡ