በቀደመው ስያሜው የአማሮ ልዩ ወረዳ በሚል የሚታወቀው አከባቢው ከአዲሱ የክልል አደረጃጀት በኃላ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ስር ከሚገኙ ዞኖች መካከል አንዱ ሆኗል፡፡ ስያሜውም ከአማሮ ልዩ ወረዳ ወደ ኮሬ ዞን ተቀይሮ የመዋቅርም፤ የስያሜም ለውጥ አድርጓል፡፡
ከልዩ ወረዳነት ወደ ዞን መዋቅር ያደገው የቀድሞ አማሮ ልዩ ወረዳ የአሁኑ ኮሬ ዞን በስሩ አንድ ከተማ አስተዳድር እና ሁለት ወረዳዎች ያሉት ሲሆን ከዚህ ቀደም በአከባቢው ነዋሪዎች ይነሳ የነበረውን የአደረጃጀት ጥያቄ ተከትሎ ይፈጠሩ የነበሩ ግጭቶች ቢቀረፉም ከአጎራባች አከባቢ ባሉ የታጠቁ ሃይሎች በዜጎች ላይ የሚቃጡ ጥቃቶች መቀጠላቸውን ነው ነዋሪዎች ለመናኸሪያ ራዲዮ ያስታወቁት፡፡
የአከባቢው ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር አማረ ገረሼ ከዚህ ቀደም ከነበረው የጸጥታ ችግር አንጻር አሁን ላይ ለውጦች ቢኖሩም ዛሬም ድረስ ህዝቡ በስጋት ውስጥ ነው የሚኖረው ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደምበዞኑ ካሉ ቀበሌዎች ዱርባደ እና ጃሎ በሚባሉት በታጣቂዎች የደረሰውን ጥቃት ሸሽተው ወደ አጎራባች ያቀኑ ነዋሪዎች ዛሬም ድረስ አለመመለሳቸውን እና ሁለቱ ቀበሌዎች ሰው የማይኖርባቸው፤ እርሻም የማይታረስባቸው ባዶ ሆነዋል ነው ያሉት፡፡
ከስፍራዉ የተፈናቁ ዜጎች ዛሬም ድረስ በአጎራባች ቀበሌዎች ድንኳን እና ሸራ ወጥረው አስቸጋሪ ህይወት እየገፉ ነው ያሉት አርሶ አደሩ ነዋሪዎቹ ወደ አከባቢያቸው የማይመለሱት አሁንም የጸጥታ ስጋት ስላለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በዚሁ የጸጥታ ችግር ምክንያት ከ2009 ዓ/ም ጀምሮ ከዲላ -አማሮ ኬሌ የሚወስደው መንገድ ለህዝብ ትራንስፖርት ዝግ እንደሆነ መቀጠሉን የገለጹት አርሶ አደሩ፤ በዚህም ምክንያት ነብሰ ጡር እናቶች እና የከፋ ህመም ያለባቸውን ዜጎች ለተጨማሪ ህክምና ወደ ሌሎች አከባቢዎች ወስዶ ለማሳከም እንደተቸገሩ ተናግረዋል፡፡
ሌላኛው ለመናኸሪያ ራዲዮ ሃሳባቸውን ያካፈሉ የአከባቢው ነዋሪ ማቲዎስ ሜጊ ከሰሞኑን በቀን 17/06/2016 ዓ/ም ማንነታቸው በውል ያልታወቁ ታጣቂ ሃይሎች ወደ ኮሬ ዞን ገብተው ከብቶችን እየጠበቀ ያለን አንድ ወጣት ገድለዋል ብለዋል፡፡
በማግስቱ በቀን 18/06/2016 ዓ/ም ማምሻ ላይ ደግሞ ወደ ዲላ በሚወስደው መንገድ የኮሬ ዞን አጎራባች በሆነው ጉጂ በተለምዶ ኮምቦልቻ ወይም ኤጀርሳ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ ታጣቂዎች ገብተው በፈጸሙት ጥቃት ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ንጹሃን ተገድለዋል ብለዋል፡፡
ስሙ ለደህንነቱ ሲባል እንዲገለጽ ያልፈለገ የአከባቢው የህክምና ባለሙያ በበኩሉ ስለ አከባቢው የጸጥታ ችግር ሲያብራራ በኮሬ ዞን እና በምዕራብ ጉጂ መካከል የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ረጅም ጊዜን ያስቆጠረ በተደጋጋሚም እርቅ በማካሄድ ሰላም ለማስፈን ጥረት ቢደረግ መፍትኤ ሊመጣለት ያልቻለ ነው ብለዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ