ባለፉት 5 ዓመታት በአገራችን የተለያዩ አከባቢዎች በሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት የበርካቶች ህይወት ማለፉ፤ ንብረት መውደሙ እና የበዙትም ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ የሰብዓዊ መብት ተቋማት የሚያወጧቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የካቲት 15/2016 ዓ/ም በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጹ ባጋራው መረጃ በኦሮሚያ ክልል በተለይም ከመስከረም 1 ቀን 2014 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ባሉት ሁለት ዓመታት ያደረገውን ክትትል እና ምርመራ መሠረት በማድረግ ከሕግ/ከፍርድ ውጪ የሆኑ እና በሲቪል ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎች በከፍተኛ ደረጃ አሳሳቢ መሆናቸውን አመላክቷል፡፡
በተለይም የክልሉ እና የፌዴራል የጸጥታ አካላት ተገቢውን ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነት ማረጋገጥን ጨምሮ ዘላቂ መፍትሔ በአስቸኳይ እንዲሰጡ ሲልም ጥሪ ማቅረቡ የሚታወስ ነው።
በአራቱ ወለጋ ዞኖች በተለያዩ ጊዜያት በንጹሃን ላይ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ከሚደርሰው ሞት በተጨማሪ በህክምና ግብዓት ዕጥረት ምክንያት የበርካቶች ህይወት እያለፈ መሆኑን የአከባቢው ነዋሪዎች ጠቁመዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን ጊዳሚ ወረዳ ነዋሪ የሆነችው ሲሳይ ቶሎሳ የቅርብ የቤተሰቧ አባል የሆነች አንዲት እናት ከሰሞኑን በአከባቢው በከፍተኛ ሁኔታ በተስፋፋው የወባ በሽታ ምክንያት በቂ ህክምና ባለማግኘቷ ህይወቷ እንዳለፈ ለመናኸሪ ራዲዮ አስታውቃለች፡፡
ምንም እንኳን የአከባቢው የህምና ባለሙያዎች ህይወቷን ለማትረፍ ጥረት ቢያደርጉም ከእነርሱ አቅም በላይ በሆነ ምክንያት የቅርብ ዘመዷን እንዳጠቻት ነው የምትገልጸው፡፡
እርሷ የምታውቃቸው 3 ህጻናት በዚሁ የወባ ወረርሽኝ ህይወታቸው ማለፉን የምትናገረው ሲሳይ፤ በአከባቢው የጸጥታ ችግር ባይኖር እንደልብ መድሐኒት ማግኘትም ሆነ በሪፈር ወደ ሌላ አከባቢ ሄዶ መታከም ይቻል ነበር ትላለች፡፡
ምላሽ ይስጡ